ፋሲለደስ

ፋሲለደስ

Wednesday, November 30, 2011

ቅድመ ምርመራ፡ ከተቋማዊ አሰራር ወደ ውስጣዊ አሰራር

የቅድመ-ምርመራ (censorship) ፅንሰ ሃሳብ የመገናኛ ብዙሃን ፅንሰ ሃሳብ ሲጠነሰስ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ተቋማዊ በሆነ መልኩ እና በተደራጀ አቀራረብ ተግባራዊ የተደረገው ግን የቆዩ ከሚባሉ ከአራቱ የፕሬስ ቲየሪዎች ሶቬት-ኮሚኒስት የፕሬስ ቲየሪ (Soviet - Communist Theory of Press) የሚባለውን የፕሬስ ፍልስፍና ያራምዱ በነበሩ ሃገራት እና መንግስታት ነው፡፡

ይህን የፕሬስ ቲየሪ ከሞላ በጎደል ለመግለፅ ያህል መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ወይንም የህዝብ ናቸው የሚል መነሻ ያለው ሲሆን በእነዚህ የመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማንኛውም ጉዳዮች የመንግስቱን ወይንም የህዝቡን (የአብዮቱን) ፍላጎት እና ጥቅም ያማከሉ መሆን እንዳለባቸው እና ይህንንም ለማረጋገጥ ቅድመ-ምርመራ አስፈላጊ ስለሆነ በተቋም ደረጃ ተደራጅቶ ማንኛውም ስርጭት እና ህትመት ለህዝብ ከመድረሱ በፊት መመርመር ይኖርበታል የሚል አንድምታ አለው፡፡

ከ1966 እስከ 1983 በሰልጣን ላይ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ይከተል የነበረው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሶሻሊዝም (ኮምዩኒዝም) ስለነበረ የመገናኛ ብዙሃን ቲየሪውም በዚህው መልኩ የተዋቀረ ነበር እናም የቅድመ-ምርመራ አሰራርን ተቋማዊ በሆነ አሰራር ተግባር ላይ አውሎት ቆይቷል፡፡ ይህ የመንግስትን አስተዳደር ሲመራ የቆየው አካል በ1983 ከወረደ በሗላ የፀደቀው አዲሱ ህገ-መንግስት ቅድመ-ምርመራን የተከለከለ ተግባር እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ሆኖም የእኔ መከራከሪያ ነጥብ ቅድመ-ምርመራ አቀራረቡን ቀየረ እንጂ አሁንም አለ የሚል ነው፡፡

በህዝብ (በመንግስት) መገናኛ ብዙሃን ስላለው ቅድመ-ምርመራ ቀድሜ ላስረዳ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ ያህል በኢትዮጵያ “የመንግስት” የሚባል መገናኛ ብዙሃን በህግ ደረጃ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዋጅ ደረጃ የህዝብ በሚል ነው የተቋቋሙት ሆኖም እንደ ማንኛውም ሃገር አብዛኛውን ግዜ የህዝብ ተቋማትን በአደራ የሚያስተዳድረው መንግስት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግስት የህዝብን አደራ በመቀበል እነዚህን ተቋማት እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን መንግስት የህዝብን አደራ እና ጥቅም ችላ በማለት ተቋማቱን በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ ለሚገኘው የአስተዳደር አካል ጥቅም በሚያደላ መልኩ እየተጠቀማባቸው ስለሚገኝ ተቋማቱ ለመንግስት ያደሉ ናቸውና “የመንግስት” መገናኛ ብዙሃን የሚል ተቀትላ እንዲሰጣቸው ሆኗል፡፡

ይህ “የመንግስት” የሚለው ተቀጥላ ግን በራሱ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከላይ ገለፅኩትን ሃሳብ የሚያጠናክር ሲሆን መንግስት የህዝብን አደራ መብላቱን እና ለህዝብ ጥቅም መዋል ያለበትን መገናኛ ብዙሃን ስልጣን ላይ ላለው አስተዳደር ጥቅም እየዋለ እንደሆነ ለመግለጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተቃውሞን መግለጫ መንገድ ሲሆን በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ጉዳዮች የህዝብን አቋም አያንጻባርቁም ፤የመንግስት ናቸው ስለዚህ አይወክሉንም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይመስላል፡፡

መንግስት በዚህ አይነት ሁኔታ የህዝብን መገናኛ ብዙሃን ሲያስተዳድር እና በስልጣን ላይ ያለውን አስተዳደር ጥቅም ለማስከበር ሲፈልግ በቅድሚያ መገናኛ ብዙሃኑን እንዲያስተዳድሩ የሚሾማቸው ሰዎች ህዝብ የሚያምንባቸውን እና በሙያቸውን ምስጉን የሆኑትን ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ የተውጣጡ እና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለድርጅታቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡትን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሁለቱንም ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት እና የሚመሩት በህዝብ የተመረጡ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ወይንም አስተዳዳሪ የተመረጡ ሹመኞች መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ እነዚህ ሹመኞች ካላቸው የመወሰን ስልጣን አንጻር የድርጅቶቹ አሰራር ስልጣን ላይ ለሚገኘው አስተዳደር በሚያደላ መልኩ እንዲሆን ተፅዕኖ የማሳደር አቅማቸውም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመገናኛ ብዙሃኑ የሚሰራጩ እና የሚተላለፉ ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት እያስተዋልን እንዳለነው በመንግስት አስተዳደር ላይ ያለውን አካል በይፋ የሚደግፉ ካልሆነ ደግሞ ቢያንስ አስተዳደሩን የማይቃወሙ ወይንም የማይተቹ እንዲሆን ቅድመ-ምርመራ ይደረጋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ የመገናኛ ብዙሃን በሁለት መንገድ የሰራተኛ (ጋዜጠኛ) ቅጥር የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው በህጋዊው አሰራር መሰረት የድርጅቱን መስፈርት የሚያሟሉ ባለሙያዎች ተወዳድረው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት የሚቀጠሩ ሲሆን ሁለተኛው የቅጥር መንገድ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ እና በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል “እጅግ ታማኝ” የሆኑ በረኛ ጋዜጠኞች (gatekeepers) የሚቀጠሩበት አሰራር ነው፡፡ እነዚህ በረኞች ትምህርታቸውም ሆነ የስራ ልምዳቸው ከመገናኛ ብዙሃን ስራ ጋር ምንም ተያያዥነት የሌለው ሲሆን ዋናው ተፈላጊ ችሎታቸው በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል ያላቸው ታማኝነት ነው፡፡

መንግስት ከህዝብ በአደራ የሚያስተዳድራቸው መገናኛ ብዙሃን ላይ የመወሰን የበላይነት ስላለው እነዚህን ታማኝ በረኞች በከፍተኛ የኤድቶሪያል ቦታዎች ያስቀመጣቸው ሲሆን ማንኛውም የሚሰራጭ እና የሚታተም ዜናም ሆነ ፕሮግራም ወይንም ሪፖርት በበረኞቹ በኩል ካልሆነ አያልፍም፡፡ በረኞቹ የመቁረጥ የመቀጠል ስልጣን ስላላቸው ማንኛውም ለህዝብ አገልጋይ ነኝ የሚል “የመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ የሰራው ዜና እና ፕሮግራም ወደደም ጠላ ለበረኞቹ መቀስ የተጋለጠ ነው፡፡ በአንድ አንድ ወቅቶች ደግሞ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው በረኞቹ የጋዜጠኛውን ሚና በመውሰድ ራሳቸው እየዘገቡ የሚገኝ ሲሆን ዘገባው በራስ ቅድመ-ምርመራ (self-censorship) የተቃኘ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በትክክለኛው መንገድ የተቀጠሩት የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችም ለራስ ቅድመ ምርመራ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በተለያየ መንገድ ከበረኞቹ እና ከተሿሚ የመገናኛ ብዙሃኑ አመራር አካላት የሚደርስባቸውን አሉታዊ ተፅኖ ለመቋቋም ያላቸው ብቸኛው አማራጭ በራሳቸው ግዜ ዘገባቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ ማድረግ ሲሆን ይህ ደግሞ የበለጠ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅድመ-ምርመራ በባህሪው በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል “ምቹ” ያልሆኑ ጉዳዮች ካሉ ያንን የሚቆጣጠር አካል የሚቆርጥ ሲሆን የራስ ቅድመ-ምርመራ ደግሞ አስፈላጊ መረጃዎችን በራስ ግዜ አለማካተት ነው፡፡

ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች “በመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ቅድመ-ምርመራ አለ ልዩነቱ መልኩን መቀየሩ ነው እላለሁ፡፡ እንዴት መልኩን ቀየረ ለሚል ጥያቄ ደግሞ ቀድሞ የነበረው የቅድመ-ምርመራ አሰራር እራሱን በቻለ ውጫዊ አካል የሚሰራ እና ተቋማዊ አቀራረብ ያለው ሲሆን አሁን የተለወጠው ነገር ይህን የቅድመ-ምርመራ አሰራር መገናኛ ብዙሃኑ የውስጥ አሰራር አድርገው እንዲወስዱት እና በጋዜጠኞቹም አመለካከት ዘንድ እንዲሰርፅ መደረጉ ነው፡፡

የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለው ቅድመ-ምርመራ በተወሰነ መልኩ “በመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ካለው የተለየ ነው፡፡ ቀለል ካለው ጉዳይ ብንነሳ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እንደምንረዳው የግል መገናኛ ብዙሃን ያላቸው የገንዘብ አቅም እና ሃብት (resource) ወሱንነት አንጻር በአስተዋወቂዎቻቸው እና ስፖንሰሮቻው ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ አብዛኞቹ የግል መገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች እና መሪዎች ሲገልፁ እንደሚስተዋለው ያሉት አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮችም ያላቸው አቅም እና ብዛት ውስን ነው፡፡ እነዚህ ውስን አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮች ደግሞ አነሱም በዙ ያሉት የግል መገናኛ ብዙሃን ይዘዋቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የአድቨርታይዝመንት ሳይንስ የእኛን በመሰለ ሃገር እጅግም ስላልሰረፀ የመገናኛ ብዙሃኑ እና አስተዋዋቂዎቹና የስፖንሰሮቹ ግንኙነት እንዲሁም መብት እና ግዴታ ግልፅ በሆነ አሰራር ሲመራ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮች የሰፋውን የመወሰን ስልጣን ሲይዙ የሚታይባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ስለሆነም መገናኛ ብዙሃኑ እነዚህን አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮችን ላለማስከፋት ይጠነቃቃሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም በአስተዋዋቂዎቻቸው እና ስፖንሰሮቻቸው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አሉታዊ ጉዳዮች ሳይዘግቡ ወይንም ተደባብሰው ሲታለፉ ይስተዋላል፡፡

ከዚህም ሌላ በተለይ ጋዜጦች በሌሎች ሃገራት እንዳለው አሰራር አብዛኛውን ገቢያቸውን የሚሰበስቡት ከአስተዋዋቂዎች እና ከስፖንሰሮች ሳይሆን ከወረቀት ሽያጭ ስለሆነ ጋዜጣቸውን ለመሸጥ ሲሉ አጀንዳ የመቅረፅ ትልቁን ሃላፊነታቸውን ለህዝቡ ወይንም ለአንባቢያቸው አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡  

ከዚህ የከፋው ግን እንደ “የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት” እንዲሁም “የፀረ-ሽብርተኝነት” የመሳሰሉ አዋጆች በመውጣታቸው፣ በነፃነት መፃፍ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ፣ የጋዜጠኞች መታሰር እና መሰደድ እየተለመደ መምጣት የመሳሰሉት ጉዳዮች ደግሞ መገናኛ ብዙሃኑንም ጋዜጠኞቹንም ለራስ ቅድመ-ምርመራ እያጋለጣቸው መሆኑን በተለያየ መንገድ ገልፀዋል፡፡ ስለዚህ በግሉም መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ቅድመ-ምርመራ ስራ ላይ እየዋለ ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ ረገድ አሁንም ህዝቡ ማግኘት የሚገባውን ጠቃሚ መረጃ እያገኘ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ በተዘረዘሩ የተለያዩ ምክንያቶች በግሉም ሆነ በመንግስት መገናኛ ብዙሃኑ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ቅድመ-ምርመራ እየተደረገ ስለሆነ በአንድ አንድ ዘገባዎች መረጃዎች እየተቆረጡ እና እተቀጠሉ ሲሆን በአንድ አንድ ዘገባዎች ደግሞ መረጃዎች ሳይካተቱ እየቀሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህዝብ በማህበራዊ፣ ምጣኔ-ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎው ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ አልያም በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ስለሚያደርገው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ይመራዋል፡፡

Tuesday, November 22, 2011

መፃፍ ጀምሬያለሁ

ከቅርብ ጊዜያት በፊት በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ሲጽፍ የቆየ አምደኛ “መፃፍ አቁሜያለሁ” በሚል ርዕስ አንድ ጠንከር ያለ አመክኖ ያለው የጽሁፍ ሃተታ አቅርቦ መጻፍ አቆመ፡፡ ይህንን ጽሁፍ ካንብበኩ በሗላ መፃፍ ብፈልግም መፃፍ ለመጀመር ብዙ ጊዜ ፈጀብኝ፡፡ ሆኖም መጻፍ ለመጀመር የቆሰቆሰኝ ዋናው ጉዳይ ይሄው ሲሆን አምደኛው መፃፍ ካቆመ በሓላ እንኳ ባለፉት ጊዜያት የሆኑት ጉዳዮች ደግሞ መፃፍ ለመጀመር ፈራ ተባ እያልኩ እንድቆይ አስገድደውኝ ሰንብተዋል፡፡ 

በእርግጥ አምደኛው መፃፍ ለማቆም የተገደደበት ዋናው ጉዳይ ምን ነበር ? 

አምደኛው በየሳምነቱ በሚፅፋቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮችን በሚተነትኑ እና በሚተቹ ፅሁፎቹ ምክንያት ያልተደሰቱ ወገኖች እንዳይፅፍ እንቅፋት ሆኑበት፡፡ ዛቻ እና ማስፈራራት ሲያበዙበት እና በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በህጋዊው መንገድ ሄዶ ሊያሸንፋቸው እንደማይችል ሲገምት እነዚህን ያልተደሰቱ ወገኖች ማስደሰት የሚቻልበት ብቸኛው አማራጭ መጻፍ በማቆም ብቻ እንደሆነ አመነ፡፡ እናም መፃፍ አቆመ፡፡ እሱ ሰላም ለማግኘት ሲል ወይንም ወህኒ ቤት እንዳይወረወር አሊያም ሕይወቱን ለማቆየት መጻፍ ማቆሙ ትክክል ነበር፡፡  

ነገር ግን ይህ አምደኛ መጻፍ በማቆሙም እርሱ እንደገለጸልን በሁለት ነገሮች ተጎዳ፤ አንድም በሕገ መንግስቱ ዋስትና ተሰቶት የነበረውን ሃሳቡን የመግለጽ ነጻነቱን ተገፈፈ፤ አንድም በመጻፍ ያገኝ የነበረው ገቢ ተቋረጠ፡፡ በእኔ እምነት የመጀመሪያው ጉዳት እጅግ የከፋ ነው ምክንያቱም በራሱ ሃገር እና በራሱ ጉዳይ ላይ የራሱ ሃገር ሰዎች ሲወስኑ እና ያሻቸውን ሲተገብሩ ዝም ብሎ መመልከትን የመሰለ የሚያስከፋ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ መንግስትም ሆነ በተዋረድ ያሉ አካላት በሚያቀርቡት ሃሳብ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ ማቅረብ ፣ ማስተካከያ ሃሳብ መሰንዘር፣ መተቸት እና መቃወም ሲቻል የቀረበው ሃሳብ እንደወረደ ተወስኖ እና ተተግብሮ ሊያደርስ የሚያስችለውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት ተካፋይ እንድንሆን ስንገደድ ከ “እናውቅላችሗለን” የዘለለ የንቀት መልዕክ የሚያስተላልፈው ቁምነገር ላይኖር ይችላል፡፡ አምደኛው ከቀበሌው ጀምሮ በአካባቢው እና በሃገሩ ጉዳይ ላይ ሲወሰን እና ሲሰለቅ አያገባህም ከተባለ ወሳኙ እና ሰላቂው አካል ሊፈጥረው በሚችለው ስህተትም የሚደርስ ጉዳትን ሊያስወግድለት ይገባል፡፡ ካልሆነ እኛ እንወስን፤ እኛ እንስራ አንተ ደግሞ ትሩፋቱን ተቋደስ ማለት ሊመጣ የሚችለው ትሩፋት ጥቅምም ቢሆን ያልተሳተፈበት ጉዳይ ነውና አያረካውም፡፡ ተሳትፎን ልናረጋግጥባቸው ከምንችላቸው የተለያዩ መንገዶች ደግሞ አንዱ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች መግለጽ ሲሆን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰዎች ሃሳባችንን እንዲደግፉም ጥሪ ማቅረብ እንችላለን፡፡ ይህ አይሆንም ካሉ ግን “እናውቅላችሗለን” የሚሉት አካላት ያወጡልን እና እንድንቀበለው ያደረጉንን ህግ ለእነሱ ጊዜ እንደማይሰራ እየነገሩን ነው ማለት ነው፡፡ 

እኔስ መጻፍ ለመጀመር ያነሳሳኝ ጉዳይ ምንድ ነው ?

ከላይ ግልፅ እንዳደረኩት በአሁኑ ወቅት ለራስ ደህንነት ሲባል መፃፍ ማቆም እጅግ ተመራጩ ውሳኔ ነው፡፡ ማሻሻያ ሃሳብ መስጠት፣ ትችት መሰንዘር፣ አዲስ ሃሳብ ማቅረብ የመሳሰሉት በአሉታዊ መልኩ ከተተረጎሙ እና ዋጋ የሚያስከፍሉ ሆነው ከተገኙ ዝም ማለቱ የተሻለው አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ አማራጭ እጅግ አስከፊ ከሆኑት ምርጫዎች በአንጻራዊ መልኩ አነስ ያለ ጉዳት ያለው አማራጭ ነው እንጂ ጉዳት የለውም አሊያም ዋጋ አያስከፍልም ማለት አይደለም፡፡ መጻፍም አለመጻፍም በዚህች ሃገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እንዲያውም አለመጻፍ የበለጠ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ልዩነቱ በመጻፋችን የምንከፍለውን ዋጋ የምናውቀው በፍጥነት ሲሆን ባለመጻፋችን የምንከፍለውን ዋጋ የምናውቀው ቀስ በቀስ መሆኑ ነው፡፡ ባለመጻፋችን ወይንም ሃሳባችን ባለመግለጻችን ቀስ በቀስ ቤተሰባችን፣ አካባቢያችን ብሎም ባጠቃላይ ሃገራችን እንደፈለጉ እንዲወስኑ እና እንዲሰልቁ በተፈቀደላቸው አካላት እጅ ስር እንደወደቀች እና በእነሱ መዘዝ እየመጣ ባለው ድህነት፣ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉት ችግሮችም ሁላችንም ጉዳት ላይ እየወደቅን እንደሆነ እያየን ነው፡፡ 

እኔ እንደምረዳው ለመብቶቻችን እንዲሁም ለነጻነታችን መታገል ማለት ነገሮች እንዲመቻቹልን መጠየቅ ሳይሆን ከምንም ነገር ተነስተን ነገሮችን ማመቻቸት ነው፡፡ የነጻነት ትሩፋት የሚጥመው የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ በአድዋ ድል የምንኮራበትን ያህል ድሉን ለማምጣት የተከፈለውን መስዋትነት እና የታለፈውን መንገድ አንዘነጋም፡፡ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲረጋገጥ እና በነጻነት መጻፍ እንድንችል ማድረግ ያለብን በብዙ ሃሳባችን መግለጽ እና በብዙ መፃፍ ነው፡፡ መፃፍ እንደተከለከልን እና ይሄም ትክክል እንዳልሆነ ልንገልፅ የምንችለው በመጻፍ ነው፡፡ ያሉን ጥቂት ፀሃፍት እንዳይፅፉ ከተከለከሉ እና የሚፅፍ ከጠፋ ማን ችግራችን፣ ብሶታችንን እና ፍላጎታችንን እንዲገልጽልን እንጠብቃለን ? 

በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በብዙ እንድንጽፍ የሚያስገድድ እንጂ ከመጻፍ እንድንቆጠብ የሚያደርገን አይመስለኝም፡፡ ሰው ስለጻፈ፣ ስለተቸ እና አማራጭ ስላቀረበ “አሸባሪ” ከተባለ ይህ አሸባሪነት አለመሆኑን የምናስረዳው በመጻፍ ነው፡፡ ሰው ተቸግሮ እና ኑሮ ከብዶት “በቃኝ!” ብሎ አደባባይ ሲወጣ “ነውጠኛ” ከተባለ ይህ ነውጠኝነት አለመሆኑን የምናስረዳው በመጻፍ ነው፡፡ ስንቃወም ከተፈረጅን፤ ስንጽፍ ከተጠረጠርን አሁንም በመጻፍ ትክክል አለመሆኑን መግለፅ ይኖርብናል፡፡ የሚጽፉት ሲታሰሩ የታሰሩት እንዲፈቱ መጻፍ አለብን፡፡ አንዱ “መጻፍ የለብህም” ሲባል ሌላው “መጻፍ መብቱ ነው” ብሎ መጻፍ አለበት:: በእርግጥ ይህንን ስንል ወይንም ይህንን ስንጽፍ እኛም ተመሳሳይ እጣ እንደሚደርስብን እርግጥ ነው ነገርግን ምርጫው እጅግ በጣም ቢከፋ ዝም ብሎ ከማለቅ እና ተናግሮ ከማለቅ የትኛው ይሻላል የሚል ነው፡፡ የሃገሬ ብሂል “እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር” የሚል ነው እናም እኔ ሃሳቤን ገልጨ የሚመጣውን መጋፈጥ መርጫለሁ፡፡

ስለጻፍኩ ምን ሊመጣብኝ ይችላል?

መጻፍ ስለጀመረኩ ብዙ ችግሮች ሊከተሉብኝ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ለነገሩ በአሁኑ ወቅት በሚጽፉ ጋዜጠኞች እና አምደኞች ዙሪያ እየደረሰ ያለውን ችግር እያየን ስለሆነ ይህ ግምቴ በአብዛኛው ወደ እውነታነት ያጋደለ ነውና “ብዙ ችግሮች ሊከተሉብኝ እንደሚችሉ አውቃለሁ” በሚል አገላለጼን ባስተካክለው ይመረጣል፡፡ በእውነት በአሁኑ ወቅት የጻፈ “አሸባሪ” እየተባለ ነው፡፡ በእርግጥ መጻፍ ሊያሸብር ይችላል፡፡ ነገር ግን መጻፍ ማንን ነው ሊያሸብር የሚችለው? መጻፍ ሊያሸብር የሚችለው በተጻፈበት ጉዳይ ዙሪያ የሚመለከተው አካል ትችቱን ማስተባበል ወይንም መቀበል የማይችል ከሆነ ነው፡፡ ማንኛውም ስራ ከትችት ሊያመልጥ አይችልም ነገር ግን አንድ ተተቺ ሁለት ምርጫዎች አሉት እነሱም ትችቱን በበቂ አመክኖአዊ አቀራረብ ማስተባበል አሊያም ትችቱን መቀበል ናቸው፡፡ ይህ ተተቺ አካል የቀረበበትን ትችት ማስተባበል የማይችል ከሆነ እና ትችቱን ለመቀበል የሚያስችል የሞራል ልዕልና ከሌለው ግን ሊሸበርም በርካታ አሉታዊ ነገሮችን በጽሁፉ እና በጸሃፊው ላይ ሊያስከትልም ይችላል፡፡

ይህ ተተቺ አካል በመጀመሪያ ሊያደርግ የሚችለው ፅሁፉን ማጣጣል እና የጸሃፊውን ስም ማጥፋት ነው፡፡ አንድ ጽሁፉ በደምሳሳው “አፍራሽ” ከተባለ ይህንን ስም የሰጠው አካል እየገነባ ያለው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ምን እየገነባ እንዳለ እና ይህ ፅሁፍ እንዴት ሊያፈርሰው እንደሚችል አይገልጽም፡፡ ይህ አመክኖአዊ አቀራረብ የሌለው ተራ ስም ማጥፋት እና ጥቁር ጥላ መቀባት ነው፡፡ ቀድሞነገር ተተቺው  የሚገነባው በዚህ ፅሁፍ የሚፈርስ ነገር ከሆነ ከመጀመሪያውም ሲገነባ የነበረው ፈራሽ ነበር ማለት ነው፡፡  

ተተቺው አካል ከስም ማጥፋት ያለፈ ችግር የማስከተል ስልጣን እና ጉልበት ያለው ከሆነ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እያየን እንዳለነው “አሸባሪ” ወይንም ሌላ ተለጣፊ ስም ሰጥቶ ሊያስፈራራ፣ ሊከስ እና ሊያስር ይችላል፡፡ ይህ በይበልጥ የሚጎዳው ተችውን ሲሆን ያለስሙ ስም ተሰጥቶት እና ያለጥፋቱ ተከሶ ሊታሰር እና ሊሰቃይ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች እና በሚጽፈው ሃሳብ ምክንያት ብሶታቸውን እየገለጸላቸው ላለው ህዝቦች ጉዳት ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይም የከፋ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

ከዚህ ሲከፋ ደግሞ ከሃገር ከማባረር እስከመግደል ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህ አሁንም ተቺውን ወይንም ጸሃፊውን (ጋዜጠኛውን) ይበልጥ ተጎጂ ያደርገዋል፡፡ መስዋዕትነቱም የከፋ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትም ግባዕተ መሬቱ ሊፈጸም ይችላል፡፡ 

ይሁን እንጂ  እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ  ጥቃቶች ሁሉ የሚሰነዘሩት በፀሃፊዎች አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ላይ ሲሆን ከዚህ እጅግ እየከፋ ሲሄድ ግን ህጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ይበልጥ እንዲጠብቁ እና ጭራሹንም ሃሳብን መግለፅ እንዳይቻል እስከመከልከል ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህ ከላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ህጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በጠቅላላው የሃገርን እና ህዝብ እድገት የሚጎዳ እና በአንድ አባገነን መሪ ጥላ ስር እንድንበረከክ የሚስገድድ ይሆናል፡፡

ሁሉንም ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶች ለመከላከል ግን አሁንም መፍትሄው ዙሪያ ገጠም ነው፡፡ ሃሳባችንን መግለጽ እንዳንከለከል ሃሳባችን መግለጽ ይኖርብናል፤ መጻፍ እንዳንከለከል መጻፍ ይኖርብናል፤ መብቶችንን ለማስከበር ለመብቶቻችን መታገል ይኖርብናል፡፡ 
 
ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ ?

በሙያየ ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ በብሄራዊው የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያ ከአራት አመት ላላነሰ ግዜ ሰርቻለሁ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመት ከመንፈቅ የሚሆኑ ጊዜያት በብሄራዊ ሬድዮ ጣቢያ የሰራሁ ሲሆን ከእነዚህ ግዜያት ውስጥም በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች በተሻለ ነጻነት ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ ቀስ በቀስ ጉዳዮች እየጠነከሩ እና “ልማታዊው” የጋዜጠኛ ሰራዊት እያየለ ሲመጣ በነጻነት መስራት የሚለው ጉዳይ እየከበደኝ እና ሌላው ቀርቶ ሙያዊ በሆኑ ጉዳዮች መግባባት እየተሳነኝ መጣሁ፡፡ በብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው በቆየሁባቸው ጥቂት ጊዜያትም የተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን የሰራሁ ቢሆንም በተጽኖ ስር ነው የቆየሁት፡፡ ከዚያ በሗላ ድርጅቱን ለቅቄ አንድ አድቮኬሲ ላይ የሚሰራ ህዝባዊ ማህበር ውስጥ ተቀጥሬ ለአንድ አመት ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅትም በተለይ ከህዝብ እና ከግሉ የመገኛኝ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጋር በቅርበት የሰራሁ ሲሆን ብዙም ግንዛቤ ያልነበረኝን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አሰራር እና እንቅስቃሴም በቅርበት ለመከታተል ችያለሁ፡፡ ከሁሉም በበለጠ ግን ይህ ግዜ ለእኔ የአርምሞ ግዜ ነበር፡፡
በዙሪያየ ያሉት በርካታዎቹ ሰዎች ጋዜጠኞች አሊያም ሙያውን የተማሩ ስለሆኑ በአንድ አንድ በሚያብሰከስኩኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ስንወያይ “ለምን አትፅፍም?” እያሉ ይወተውቱኛል፡፡ እርግጥ ነው ልጽፍ የምችልባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩኝ ነገር ግን በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምን ያህል የተሻለ መረጃ እና ግንዛቤ አለኝ? ብሎም እነዚህን ጉዳዮች ምን ያህል አመክኖአዊ አቀራረብ ባለው መልኩ ልተነትናቸው እችላለሁ የሚለው ነበር ስጋቴ፡፡ ከጓደኞቼ የገጠመኝ ትልቁ መከራከሪያ ነጥብ ግን እነዚህን ሃሳቦቼን ዘርዝሬ ካላቀረብኳቸው ትክክል ስለመሆኔ እና ስለመሳሳቴ ማስረጃ እንደሌለ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ከላይ እንዳሰፈርኩት ካልተተቸሁ ልማር እንደማልችል አምናለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት መጻፍ ለመጀመር ሃሳቦቼን ሳደራጅ እና መረጃዎችን ስሰበስብ ጊዜ ፈጅቶብኛል፡፡ በዚህ ጊዜ የተገነዘብኩትን ጉዳይ ለመግለፅ ግን መጻፍ ያልጀመርኩት በእውነትም ፈርቼ ስለነበር ነው፡፡ አንድም ጥቃት እንዳይሰነዘርብኝ ፈርቼ ነበር ፤ አንድም የሰላ ትችት እንዳይሰነዘርብኝ ፈርቼ ነበር፡፡ 

ከዚህ ባለፈ ልጽፍ በምችለው ነገር ከስሜታዊነት ለመጽዳት እና ሰዎችን ላለመወንጀል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ መረጃዎቼ በአስተያየት እና በእውነታ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆን እና ልሰጥ የምችለው ትንታኔ ከእነዚህ የተነሳ እንዲሆን ሙያየም ያስገድደኛል፡፡