የቅድመ-ምርመራ (censorship) ፅንሰ ሃሳብ የመገናኛ ብዙሃን ፅንሰ ሃሳብ ሲጠነሰስ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ተቋማዊ በሆነ መልኩ እና በተደራጀ አቀራረብ ተግባራዊ የተደረገው ግን የቆዩ ከሚባሉ ከአራቱ የፕሬስ ቲየሪዎች ሶቬት-ኮሚኒስት የፕሬስ ቲየሪ (Soviet - Communist Theory of Press) የሚባለውን የፕሬስ ፍልስፍና ያራምዱ በነበሩ ሃገራት እና መንግስታት ነው፡፡
ይህን የፕሬስ ቲየሪ ከሞላ በጎደል ለመግለፅ ያህል መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ወይንም የህዝብ ናቸው የሚል መነሻ ያለው ሲሆን በእነዚህ የመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማንኛውም ጉዳዮች የመንግስቱን ወይንም የህዝቡን (የአብዮቱን) ፍላጎት እና ጥቅም ያማከሉ መሆን እንዳለባቸው እና ይህንንም ለማረጋገጥ ቅድመ-ምርመራ አስፈላጊ ስለሆነ በተቋም ደረጃ ተደራጅቶ ማንኛውም ስርጭት እና ህትመት ለህዝብ ከመድረሱ በፊት መመርመር ይኖርበታል የሚል አንድምታ አለው፡፡
ከ1966 እስከ 1983 በሰልጣን ላይ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ይከተል የነበረው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሶሻሊዝም (ኮምዩኒዝም) ስለነበረ የመገናኛ ብዙሃን ቲየሪውም በዚህው መልኩ የተዋቀረ ነበር እናም የቅድመ-ምርመራ አሰራርን ተቋማዊ በሆነ አሰራር ተግባር ላይ አውሎት ቆይቷል፡፡ ይህ የመንግስትን አስተዳደር ሲመራ የቆየው አካል በ1983 ከወረደ በሗላ የፀደቀው አዲሱ ህገ-መንግስት ቅድመ-ምርመራን የተከለከለ ተግባር እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ሆኖም የእኔ መከራከሪያ ነጥብ ቅድመ-ምርመራ አቀራረቡን ቀየረ እንጂ አሁንም አለ የሚል ነው፡፡
በህዝብ (በመንግስት) መገናኛ ብዙሃን ስላለው ቅድመ-ምርመራ ቀድሜ ላስረዳ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ ያህል በኢትዮጵያ “የመንግስት” የሚባል መገናኛ ብዙሃን በህግ ደረጃ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዋጅ ደረጃ የህዝብ በሚል ነው የተቋቋሙት ሆኖም እንደ ማንኛውም ሃገር አብዛኛውን ግዜ የህዝብ ተቋማትን በአደራ የሚያስተዳድረው መንግስት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግስት የህዝብን አደራ በመቀበል እነዚህን ተቋማት እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን መንግስት የህዝብን አደራ እና ጥቅም ችላ በማለት ተቋማቱን በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ ለሚገኘው የአስተዳደር አካል ጥቅም በሚያደላ መልኩ እየተጠቀማባቸው ስለሚገኝ ተቋማቱ ለመንግስት ያደሉ ናቸውና “የመንግስት” መገናኛ ብዙሃን የሚል ተቀትላ እንዲሰጣቸው ሆኗል፡፡
ይህ “የመንግስት” የሚለው ተቀጥላ ግን በራሱ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከላይ ገለፅኩትን ሃሳብ የሚያጠናክር ሲሆን መንግስት የህዝብን አደራ መብላቱን እና ለህዝብ ጥቅም መዋል ያለበትን መገናኛ ብዙሃን ስልጣን ላይ ላለው አስተዳደር ጥቅም እየዋለ እንደሆነ ለመግለጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተቃውሞን መግለጫ መንገድ ሲሆን በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ጉዳዮች የህዝብን አቋም አያንጻባርቁም ፤የመንግስት ናቸው ስለዚህ አይወክሉንም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይመስላል፡፡
መንግስት በዚህ አይነት ሁኔታ የህዝብን መገናኛ ብዙሃን ሲያስተዳድር እና በስልጣን ላይ ያለውን አስተዳደር ጥቅም ለማስከበር ሲፈልግ በቅድሚያ መገናኛ ብዙሃኑን እንዲያስተዳድሩ የሚሾማቸው ሰዎች ህዝብ የሚያምንባቸውን እና በሙያቸውን ምስጉን የሆኑትን ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ የተውጣጡ እና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለድርጅታቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡትን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሁለቱንም ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት እና የሚመሩት በህዝብ የተመረጡ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ወይንም አስተዳዳሪ የተመረጡ ሹመኞች መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ እነዚህ ሹመኞች ካላቸው የመወሰን ስልጣን አንጻር የድርጅቶቹ አሰራር ስልጣን ላይ ለሚገኘው አስተዳደር በሚያደላ መልኩ እንዲሆን ተፅዕኖ የማሳደር አቅማቸውም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመገናኛ ብዙሃኑ የሚሰራጩ እና የሚተላለፉ ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት እያስተዋልን እንዳለነው በመንግስት አስተዳደር ላይ ያለውን አካል በይፋ የሚደግፉ ካልሆነ ደግሞ ቢያንስ አስተዳደሩን የማይቃወሙ ወይንም የማይተቹ እንዲሆን ቅድመ-ምርመራ ይደረጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ የመገናኛ ብዙሃን በሁለት መንገድ የሰራተኛ (ጋዜጠኛ) ቅጥር የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው በህጋዊው አሰራር መሰረት የድርጅቱን መስፈርት የሚያሟሉ ባለሙያዎች ተወዳድረው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት የሚቀጠሩ ሲሆን ሁለተኛው የቅጥር መንገድ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ እና በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል “እጅግ ታማኝ” የሆኑ በረኛ ጋዜጠኞች (gatekeepers) የሚቀጠሩበት አሰራር ነው፡፡ እነዚህ በረኞች ትምህርታቸውም ሆነ የስራ ልምዳቸው ከመገናኛ ብዙሃን ስራ ጋር ምንም ተያያዥነት የሌለው ሲሆን ዋናው ተፈላጊ ችሎታቸው በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል ያላቸው ታማኝነት ነው፡፡
መንግስት ከህዝብ በአደራ የሚያስተዳድራቸው መገናኛ ብዙሃን ላይ የመወሰን የበላይነት ስላለው እነዚህን ታማኝ በረኞች በከፍተኛ የኤድቶሪያል ቦታዎች ያስቀመጣቸው ሲሆን ማንኛውም የሚሰራጭ እና የሚታተም ዜናም ሆነ ፕሮግራም ወይንም ሪፖርት በበረኞቹ በኩል ካልሆነ አያልፍም፡፡ በረኞቹ የመቁረጥ የመቀጠል ስልጣን ስላላቸው ማንኛውም ለህዝብ አገልጋይ ነኝ የሚል “የመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ የሰራው ዜና እና ፕሮግራም ወደደም ጠላ ለበረኞቹ መቀስ የተጋለጠ ነው፡፡ በአንድ አንድ ወቅቶች ደግሞ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው በረኞቹ የጋዜጠኛውን ሚና በመውሰድ ራሳቸው እየዘገቡ የሚገኝ ሲሆን ዘገባው በራስ ቅድመ-ምርመራ (self-censorship) የተቃኘ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በትክክለኛው መንገድ የተቀጠሩት የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችም ለራስ ቅድመ ምርመራ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በተለያየ መንገድ ከበረኞቹ እና ከተሿሚ የመገናኛ ብዙሃኑ አመራር አካላት የሚደርስባቸውን አሉታዊ ተፅኖ ለመቋቋም ያላቸው ብቸኛው አማራጭ በራሳቸው ግዜ ዘገባቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ ማድረግ ሲሆን ይህ ደግሞ የበለጠ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅድመ-ምርመራ በባህሪው በመንግስት አስተዳደር ላይ ለሚገኘው አካል “ምቹ” ያልሆኑ ጉዳዮች ካሉ ያንን የሚቆጣጠር አካል የሚቆርጥ ሲሆን የራስ ቅድመ-ምርመራ ደግሞ አስፈላጊ መረጃዎችን በራስ ግዜ አለማካተት ነው፡፡
ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች “በመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ቅድመ-ምርመራ አለ ልዩነቱ መልኩን መቀየሩ ነው እላለሁ፡፡ እንዴት መልኩን ቀየረ ለሚል ጥያቄ ደግሞ ቀድሞ የነበረው የቅድመ-ምርመራ አሰራር እራሱን በቻለ ውጫዊ አካል የሚሰራ እና ተቋማዊ አቀራረብ ያለው ሲሆን አሁን የተለወጠው ነገር ይህን የቅድመ-ምርመራ አሰራር መገናኛ ብዙሃኑ የውስጥ አሰራር አድርገው እንዲወስዱት እና በጋዜጠኞቹም አመለካከት ዘንድ እንዲሰርፅ መደረጉ ነው፡፡
የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለው ቅድመ-ምርመራ በተወሰነ መልኩ “በመንግስት” መገናኛ ብዙሃን ካለው የተለየ ነው፡፡ ቀለል ካለው ጉዳይ ብንነሳ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እንደምንረዳው የግል መገናኛ ብዙሃን ያላቸው የገንዘብ አቅም እና ሃብት (resource) ወሱንነት አንጻር በአስተዋወቂዎቻቸው እና ስፖንሰሮቻው ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ አብዛኞቹ የግል መገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች እና መሪዎች ሲገልፁ እንደሚስተዋለው ያሉት አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮችም ያላቸው አቅም እና ብዛት ውስን ነው፡፡ እነዚህ ውስን አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮች ደግሞ አነሱም በዙ ያሉት የግል መገናኛ ብዙሃን ይዘዋቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የአድቨርታይዝመንት ሳይንስ የእኛን በመሰለ ሃገር እጅግም ስላልሰረፀ የመገናኛ ብዙሃኑ እና አስተዋዋቂዎቹና የስፖንሰሮቹ ግንኙነት እንዲሁም መብት እና ግዴታ ግልፅ በሆነ አሰራር ሲመራ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮች የሰፋውን የመወሰን ስልጣን ሲይዙ የሚታይባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ስለሆነም መገናኛ ብዙሃኑ እነዚህን አስተዋዋቂዎች እና ስፖንሰሮችን ላለማስከፋት ይጠነቃቃሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም በአስተዋዋቂዎቻቸው እና ስፖንሰሮቻቸው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አሉታዊ ጉዳዮች ሳይዘግቡ ወይንም ተደባብሰው ሲታለፉ ይስተዋላል፡፡
ከዚህም ሌላ በተለይ ጋዜጦች በሌሎች ሃገራት እንዳለው አሰራር አብዛኛውን ገቢያቸውን የሚሰበስቡት ከአስተዋዋቂዎች እና ከስፖንሰሮች ሳይሆን ከወረቀት ሽያጭ ስለሆነ ጋዜጣቸውን ለመሸጥ ሲሉ አጀንዳ የመቅረፅ ትልቁን ሃላፊነታቸውን ለህዝቡ ወይንም ለአንባቢያቸው አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡
ከዚህ የከፋው ግን እንደ “የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት” እንዲሁም “የፀረ-ሽብርተኝነት” የመሳሰሉ አዋጆች በመውጣታቸው፣ በነፃነት መፃፍ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ፣ የጋዜጠኞች መታሰር እና መሰደድ እየተለመደ መምጣት የመሳሰሉት ጉዳዮች ደግሞ መገናኛ ብዙሃኑንም ጋዜጠኞቹንም ለራስ ቅድመ-ምርመራ እያጋለጣቸው መሆኑን በተለያየ መንገድ ገልፀዋል፡፡ ስለዚህ በግሉም መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ቅድመ-ምርመራ ስራ ላይ እየዋለ ነው ማለት ነው፡፡
በዚህ ረገድ አሁንም ህዝቡ ማግኘት የሚገባውን ጠቃሚ መረጃ እያገኘ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ በተዘረዘሩ የተለያዩ ምክንያቶች በግሉም ሆነ በመንግስት መገናኛ ብዙሃኑ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ቅድመ-ምርመራ እየተደረገ ስለሆነ በአንድ አንድ ዘገባዎች መረጃዎች እየተቆረጡ እና እተቀጠሉ ሲሆን በአንድ አንድ ዘገባዎች ደግሞ መረጃዎች ሳይካተቱ እየቀሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህዝብ በማህበራዊ፣ ምጣኔ-ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎው ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ አልያም በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ስለሚያደርገው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ይመራዋል፡፡
No comments:
Post a Comment