በዓለምዓቀፍ
ደረጃ ያለውን የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በመምራት ላይ የሚገኘው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ዓይነቶችን ጥቃቅን ሙስና፣ ግዙፍ
ሙስና እና ፖለቲካዊ ሙስና በሚል በሶስት ይከፍላቸዋል፡፡
እንደ
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ትርጉም አሰጣጥ ጥቃቅን ሙስና ማለት በህግ የተሰጠን ሃላፊነት በማንኛውም መንገድ ያለአግባብ መጠቀም
ሲሆን መሰረታዊ ግልጋሎቶችን ለማግኘት ዜጎች ከተለያዩ በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት
ግንኙነት ሊፈጠር የሚችል አድሎአዊ አሰራርን ያጠቃልላል፡፡
በሌላ
በኩል ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ የመንግስት አካላት የመንግስት ሃብትን ለመመዝበር በሚያመች መልኩ ፖሊሲዎችን እና ህጎችን ያለአግባብ
ለመተርጎም ሲሞክሩ እና የመንግስትን መሰረታዊ አቋም እንዲፋለስ ሲያደርጉ ግዙፍ ሙስና እንደሚሆን ድርጅቱ ያስረዳል፡፡
ማንኛውም
አይነት የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ በሚል በገንዘብ ወይንም በአይነት የሚፈጸም ሙስና ፖለቲካዊ ሙስና ሲሆን ፖለቲካዊ
ሙስና የሚፈፀመው
ደግሞ በአንድ
ሀገር የፖለቲካ አናት
ላይ በሚገኙና በሀገር
ሀብት ስርጭት ወይም
ታላላቅ ፖሊሲዎችና
ህጎች ላይ ለመወሰን
ሥልጣንና ኃላፊነት ባላቸው
አካላት ነው፡፡
በዚህ የስልጣን
ደረጃ የሚገኙ ግለሰቦች
ወይንም አካላት ፖለቲካዊ ሙስና የሚፈጽሙት አንድም ሀብት
ለማካበት ሲሆን አንድም
ደግሞ የስልጣን ቆይታ
ጊዜያቸውን ለማራዘም ሊሆን
ይችላል ፡፡ ይህ
ማለት በአንድ
በኩል ስልጣንን ተጠቅመው
ያለአግባብ ሃብት ሲያከማቹ
በሌላ መንገድ ደግሞ
የህዝብንና የመንግስትን
ገንዘብ በመጠቀም የተደላደለ
የስልጣን ደረጃ ላይ
ተቀምጦ ለመቆየት ያስችላቸዋል፡፡
ሆኖም
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልም ሆነ ሌሎች በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት በሙስና
ዙሪያ የሚወጡ በርካታ
ጽሁፎች የሚያተኩሩት
ስልጣንን ተጠቅሞ ያለአግባብ
ሃብት ማከማቸት ላይ
ሲሆን “ፖለቲካዊ ሙስና ስልጣንን
ለማራዘም” የሚለው ጉዳይ ግን በደንብ
ያልታየና ጠለቅ ያለ
ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡
ፅሁፎች ሲባል በጥናት መልክ የተዘጋጁ፣ ለውይይት መነሻ የሚቀርቡ
አሊያም በመገናኛ ብዙሃን የሚዘገቡትን የሚያካትት ሲሆን የዚህ ችግር በሃገራችንም ይስተዋላል፡፡
በኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ
በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተለያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት ፅሁፍ አቅራቢ የነበሩት
እንግዳ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በሙስና ዙሪያ የሚሰሩት ዘገባ በአብዛኛው ሃላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም ሃብት ምዝበራ ላይ
ያተኮረ ሲሆን ያለአግባብ ስልጣንን ለማራዘም የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ትኩረት የተሰጠው እንዳልሆነ ተችተዋል፡፡
በዚህ አስተያየት መሰረት ሁለት መላምቶችን ማስቀመጥ የሚቻል ሲሆን የመጀመሪያው ስልጣንን ያለአግባብ
ለማራዘም መሞከር በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ እንደ ፖሊካዊ ሙስና አለመታየቱ ነው፡፡ ሁለተኛው መላምት ደግሞ ፖለቲካዊ ሙስና መልካም
አስተዳደር በማስፈን ሂደትም ሆነ በልማት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ መገናኛ ብዙሃን ባለመረዳታቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
የህዝብ
ሃብትን በመመዝበር
የስልጣን እድሜን ለማስረዘም
የሚደረገው ጥረት ብዙውን
ጊዜ አድሎን ወይንም
ጥቅምን ያማከለ የፖለቲካ
ስርዓት ይፈጥራል፡፡
ይህ የፖለቲካ ሙስና
የፖለቲካ አመለካከትን ያማከለ
የገንዘብ፣ የእቃ፣
የጥቅማ ጥቅም፣ የእድሎችና
ገፈቶች ክፍፍልን ያካትታል
፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና
ባጠቃላይ በዋናነት ሊያስከትላቸው
የሚችለው ጉዳቶች የተቋማት
ወድቀት፣ ስልጣን በዘፈቀደ
መንገድ መያዝ፣ የአምባገነንነት
ባህሪን መላበስና የዜጎች
ነጻነት መገደብ ናቸው
፡፡
ፖለቲካዊ
ሙስናን ቴክኒካዊ ወይንም
ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ
ብቻ ማስቆም አሊያም
መቀነስ እንደማይቻል ድረ-ገፅን መሰረት ያደረገው እና በጸረ-ሙስና እንቅስቃሴ
ዙሪያ ለሚሰሩ ተቋማት እንደ መረጃ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለው u4 የተባለ ተቋም ይገልጻል፡፡ እንደ u4 መረጃ ፖለቲካዊ ሙስና
ራሱን እንደቻለ አንድ
የገበያ ችግር ወይንም
የተበላሸ የአስተዳደር
ሥርዓት ተደርጎ ሊታይም
አይችልም ፡፡
የፖለቲካዊ
ሙስናን ለመዋጋት ባለድርሻዎች
የራሳቸውን ውስን ሚና
የሚጫወቱበትን መንገድ ማፈላለግ
የሚያስችል የፖለቲካ ባህሪ
ያለው መፍትሄ ያሻል
፡፡ የችግሩን ምንጭ
ማድረቅ ማለትም ፖለቲከኞች
በፖለቲካ ስርዓቱ አግባብ
ባልሆነ መንገድ የግል
ጥቅማቸውን ሊያስከብሩ
የሚችሉበትን መንገድ ማጥበብ
ብሎም ለፖለቲካ ሙስና
ሊኖር የሚችለውን
ፍላጎት መቀነስ አንዱ
አማራጭ ሊሆን ይችላል
፡፡ እዚህ ላይ
ከባድ ፈተና ሊሆን የሚችለው
ለህገወጥ ምዝበራ ክፍት
የሆኑ ቀዳዳዎችን
እንዴት መድፈን ይቻላል
የሚለውና እንዴት ግልጽነትን፣
ተጠያቂነትንና የውስጥ ቁጥጥር
ስርዓትን መፍጠር ይቻላል
የሚሉት ናቸው፡፡
በዋናነት የህዝብን ጥቅም ማስከበር
ስለሆነ ዓላማቸው መገናኛ ብዙሃን በተለይ በዚህ ረገድ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የራሳቸውን የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት
የሚያስችል ሰፊ እና እምቅ ሃይል እንዳላቸው እሙን ነው፡፡
ነገርግን ይህም እንዳይሆን ፖለቲካዊ
ሙሰኞች የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን በመገደብ የራሳቸውን ደህንነት
እና የስልጣን መደላደል ሊያመቻቹ የሚችሉ ሲሆን ካላቸው የመወሰን አቅም ከፍተኛነት አንጻር መገናኛ ብዙሃኑንም ሆነ ጋዜጠኞችን ሊገዳደሩ
ይችላሉ፡፡
የምርመራ ጋዜጠኝነት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የሚታየው እዚህ ላይ ነው፡፡
የምርመራ ጋዜጠኝነት ከተለመደው የጋዜጠኝነት ሙያ የሚለየው እጅግ ስልታዊ በሆነ አካሄድ
በሚዘገበው ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምልከታ፣ ዳሰሳ እና ትንተና ስለሚጠይቅ ሲሆን ሙስናን ለመዋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊጫወት ይችላል፡፡
እንዲህ አይነቱ የጋዜጠኝነት ሙያ ብዙውን ጊዜ የሚያተኩረው በከፍተኛ ደረጃ የተሰሩ ሙስናዎችን እንዲሁም ትላልቅ ድርጅቶች የሰሯቸውን
ከፍተኛ ጥፋቶች በጥልቀት መርምሮ ይፋ ማውጣት ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም የተወሳሰቡ እና የተደበቁ ሙስናዎችን የሚያጋልጥ
ሲሆን በመጨረሻም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ሆኖም
የምርመራ ጋዜጠኝነት እና በዘርፉ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በርካታ ችግሮች ያሉባቸው ሲሆን ችግሮቹ ህልውናቸውን እስከመፈታተን እና የስራቸውን
ጥራት እስከማበላሸት የሚያደርሱ ናቸው፡፡ በምርመራ ጋዜጠኝነት ዙሪያ ያለው ዋነኛ አጠያያቂ ጉዳይ ስራውን ለሚያከናውኑ ጋዜጠኞች
እና ጥቆማ አቅራቢዎች በቂ ከለላ ሊሰጥ የሚችል ህግ አለመኖር ወይንም ያለው ህግ እና ተፈጻሚነት ደካማ መሆን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የአቅም ውሱንነት፣ የፋይናንስ እጥረት እና
መገናኛ ብዙሃኑ ውስጥ ሙስና መበራከት በሀገራችን እንዲያውም የለም የተባለውን የምርመራ ጋዜጠኝነት የበለጠ ድራሹ እንዲጠፋ እያደረገው
ነው፡፡
በዚህም
ምክንያት ፖለቲካዊ ሙስና መድሃኒት ያልተገኘለት ከባድ የሃገራችን ችግር ሆኖ እንዲቆይ ግድ የሚል ሲሆን የፖለቲካዊ ሙስና መጠንከር
የምርመራ ጋዜጠኝነትን እንደሚያዳክመው ሁሉ የምርመራ ጋዜጠኝነት መጠንከር ደግሞ ፖለቲካዊ ሙስናን እንደሚያዳክመው ግን እሙን ነው፡፡