በመሰረቱ ስፖርት ሲባል ባህላዊውንም ዘመናዊውንም
ጨምሮ አብዛኛዎቻችን ልንዘረዝራቸው የምንችላቸው የአካል እንቅስቃሴ እና ጥልቅ እሳቤን የሚጠይቁ ሁሉንም አይነት ጨዋታዎች ያጠቃልላል፡፡
ከመገናኛ ብዙሃን ፍላጎት አንጻር ስፖርት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የቆየ የመዝናኛ ፕሮግራም ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ ከመዝናኛነትም
ያለፈ ጉዳይን እየሆነ ይገኛል፡፡
ስፖርት እንደ አንድ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና
ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ሲሆን ሊሰጠው የሚገባው ግምትም ያን ያህል እየከበደ
መጥቷል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮች ብቻ የሚተነትኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ
ሁሉ ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች፣ ሬድዮኖች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ-ገጾች እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በርካታ
ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ስፖርታዊ ጉዳይን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች
እና ድረ-ገጾች ያሉ ሲሆን በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ለስፖርታዊ ጉዳዮች ከሌሎቹ ርዕሰ-ጉዳዮች አንጻር ተመጣጣኝ ባይሆንም
ፍትሃዊ የአየር ሰዓት ተመድቧል ማለት ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ ግን ከበርካታ በዙሪያየ ካሉ ሰዎች የተለያዩ
አስተያየቶችን አደምጣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዋናው ጉዳያቸው ስፖርት ይመስል ወሪያቸው ሁሉ ስፖርት ሆነ የሚሉ አሉ፡፡
በእውነትም ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮችን እና ስፖርትን በአንድ ላይ ጨፍልቆ ለሚያቀርብ የሬድዮ ወይንም የቴሌቪዥን
ጣቢያ ስፖርት ይህን ያህል የአየር ሰዓት ማግኘቱ የቀደመውን አስተያየት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ነገርግን ስፖርት በራሱ ካለው ዘርፈ
ብዙ ጉዳይ አንፃር እንዲያውም ከላይ ከጠቀስኳቸው ሶስቱ ዋና ጉዳዮች ጋር መጨፍለቁ ተገቢዉን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል የሚል
ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ እንደሌሎች ሃገራት ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚያቀርቡ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አለመኖራቸው ተጎጂ
እንዳደረገን አምናለሁ፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሃገር ቤት እየተተገበረ ያለው
የስፖርት ጋዜጠኝነት ምን ያህል ሙያዊ እና ስነምግባራዊ ነው ለሚለው እኔም በርካታ አሉታዊ አስተያየቶች አሉኝ፡፡
በአብዛኛው ለሃገርቤት መገናኛ ብዙሃን ስፖርት ማለት የእግር
ኳስ ጨዋታ ሆኗል ያውም የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ ካለው አዝናኝነት፣ ከተመልካቹ ብዛት እና ከሚያንቀሳቅሰው
ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር በጋዜጣ ላይ የሰፋውን ቦታ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የበዛውን የአየር ሰዓት ቢይዝ
የጎላ ጥያቄ ላያስነሳ ይችላል፡፡ ሆኖም በእኔ ዳሰሳዊ ግምት በተለያየዩ የኤፍ ኤም እና የኤ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ከሚቀርቡ የስፖርት
ዝግጅቶች ብዙውን ግዜ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ እና አንድ አንድ ግዜ ከዘጠና በመቶ በላይ የእግር ኳስ ጉዳይ የሚተነተን ሲሆን ከዚህም የሚበዛው የአውሮፓ የእግር ኳስ
ክለቦች ጨዋታ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት በተለያዩ ጉዳዮች ተፅዕኖ ሊሆን
ይችላል አንደኛ የእግር ኳስ በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ከሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተሻለ አዝናኝ
ነው ተብሎ ስለሚገመት፤ ሁለተኛ በሃገር ውስጥ አብዛኛው የስፖርት አድናቂ ማህበረሰብ የእግር ኳስን በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች
የእግር ኳስ ጨዋታን የበለጠ ይወዳል ተብሎ ስለሚገመት፣ ሦስተኛ ደግሞ በተለይ ከአውሮፓ ሃገራት መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ እጅግ
ብዛት ያላቸው እና የየክለቦቻቸውን ሁኔታ የሚተነትኑ መረጃዎች በተትረፈረፈ ሁኔታ ማግኘት መቻሉ የጋዜጠኞችን ትኩረት በመሳቡ ሊሆን
ይችላል፡፡ በእነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኝ ሆኗል፡፡
የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ መተንተኑ ባይከፋም
መገናኛ ብዙሃኑን በሚከታተለው ህብረተሰብ ዘንድ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ግን የተስተዋለ አሊያም በደንብ የተጠና አይመስለኝም፡፡
መረጃ ስለተገኘ ዝም ብሎ መተንተን ወይንም በመገናኛ ብዙሃን ማቅረብ ፋይዳው ምንድነው? እከሌ የሚባለው ቡድን አሸነፈ ወይንም ተሸነፈ
መባሉ መልካም ሆኖ ሳለ የእከሌው ቡድን ተጫዋች ወይንም አሰልጣኝ እንዲህ አለ ተብሎ መቅረቡ ለኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ተከታታዮች
ጥቅሙ ምንድን ነው? እሱ እንዲህ ስላለ እና ምን ይሁን? ከዘገባው ጀርባ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚቻል ከሆነ የዘገባው ፋይዳ
(impact) ተለይቷል ማለት ነው ሆኖም የአብዛኞቹ ዘገባዎች ፋይዳ ምን ስለመሆኑ አቅራቢዎቹም ተከታታዮቹም ስለማወቃቸው እርግጠኛ
አይደለሁም፡፡
በሚገርም ሁኔታ በአንድ አንድ የሃገር ውስጥ የስፖርት
ጋዜጦች ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ጉዳዮች የሚቀርብባቸው ሲሆን የጋዜጣው ባለቤት አቋሙን በሚገልጽበት
ኤድቶሪያል ላይ ግን ስለኢትዮጵያ ስፖርት አቋሙን ያቀርባል፡፡ በዘገቡት ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ሙያዊም ሞራላዊም ሲሆን ባልዘገቡት
ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ግን አሁንም የዘገባ ፋይዳ የቱን ያህል እንደሆነ አለመረዳት ይመስለኛል፡፡
የሃገር ውስጥ ስፖርት የእግር ኳሱን ጨምሮ በአብዛኞቹ
ስፖርታዊ ጉዳዮችን በሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡ ይሄን ጉዳይ ቢያቀርቡ የተሻለ ለውጥ ማምጣት
ስለመቻላቸውም እርግጠኞች አይደሉም፡፡ በአንድ ወቅት የደከመ ወይንም የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግብ ሚናቸውን ባልለየ መልኩ ከመጯጯህ
እና አስተያየት ከመስጠት ባለፈ በአዘቦት ግዜያት የሃገር ውስጥ ስፖርት በሃገር ውስጥ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ችላ እንደተባለ
ነው፡፡
ከዘህ በተረፈ ግን የሩጫ፣ የቴንስ፣ የቦሊቦል፣ የጎልፍ፣
የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የገበጣ ጨዋታ እና የሌሎችም ስፖርታዊ ጨዋታዎች አድናቂዎች እነዚህን ዘገባዎች ከሃገር ውስጥ መገናኛ
ብዙሃን ለማግኘት ቢያንስ በወር አንዴ መጠበቅ አሊያም ራሳቸው ጨዋታዎቹ የሚካሄዱባቸው ቦታዎች በመሄድ ከቦታው መረጃ ማግኘት ግድ
ሳይላቸው አልቀረም፡፡
የስፖርት እና የጥበብ (ART) ጋዜጠኝነት ከሌላው
የጋዜጠኝነት ሙያ በተለየ እና በተሻለ መልኩ ለጋዜጠኛው የሚሰጠው ነጻነት እና መብት አለ እሱም ሙያው ጋዜጠኞቹ በሚዘግቡት ጉዳይ
ላይ የግል አስተያየታቸውን እንዲሁም ትችታቸውን በማካተት ማቅረብ እንዲችሉ መፍቀዱ ነው፡፡
ይህ ጋዜጠኞቹ ሊያቀርቡት የሚችሉት የግል አስተያየት
እና ትችት በጉዳዮቹ መሰረታዊ ሃሳብ እና እውነታ ላይ ተነስተው የተደራጀ እና ከስሜት የፀዳ ሃሳብ ከመስጠት ስሜታዊ አስተያየት
እስከመስጠት እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ ስፖርት ጋዜጠኛ አንድን የእግር ኳስ ተጫዋች “ይህ ተጫዋች የእግር ኳስ ከሚጫወት
ቢያርስ ይሻል ነበር” እስከሚል ስሜታዊ አስተያየት ቢሰጥ በህግም በሥም ማጥፋት ሊያስጠይቀው አይችልም፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስፖርት የሚሉት
እግር ኳስ ብቻ እንደሆነ እና እግር ኳሱም ያለው በአውሮፓ ክለቦች ዘንድ እንደሆነ እንቀበለው ብንልም እንኳ ይህንኑ የአውሮፓ ክለቦች
እግር ኳስ የሚዘግቡበት መንገድም ግን የተሳሳተ ነው፡፡
የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል አንድ አንዶቹ የስፖርት
ጋዜጠኞች “እኔ ብሆን ኖሮ ተጨዋቹ እንዲህ አደርግ ነበር፤ እኔ ብሆን ኖሮ አሰልጣኙ እንዲህ አይነቱን የጨዋታ አይነት እከተል ነበር”
የመሳሰሉትን አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ይሄ የጋዜጠኝነት ሚናን አለመለየት ነው፡፡ አሱ ጨዋታው እንዴት እንደተካሄደ፣ ምን
ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደነበሩት፣ ምን ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር መረጃ አጠናቅሮ እና የራሱን አስተያየት አክሎ ሊነግረን ሲገባ
እርሱ ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማውራቱ ማንነቱን ያለመለየቱ ችግር ይመስለኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስፖርት ዘገባዎች ላይ
እውነታም አስተያየትም ያሆኑ ጉዳዮች ሲቀርቡ ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል “እከሌ የተባለው አሰልጣኝ እንደዚህ አስቦ ነበር፣ እከሌ
የተባለው ተጫዋች ፍላጎት እንዲህ ነበር” የመሳሰሉ ነገሮች በስፖርት ጋዜጦች ተፅፈው ማንበብ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች
ሲነገሩ ማዳመጥ አዲስ አይደለም፡፡ በዚህ ግዜ እኔ የጋዜጠኞቹን ሰብዓዊ ፍጡርነት እጠራጠራለሁ፡፡ አንድ አሰልጣኝ የተናገረውን ለማወቅ
ጋዜጠኛ መሆን በቂ ሲሆን ይህ አሰልጣኝ ያሰበውን ለማወቅ ግን አንድም አሰልጣኙ ይህን አስቢያለሁ ብሎ መናገር አለበት አንድም ጋዜጠኛው
ሰው የሚያሰበውን የሚያውቅ የተለየ ፍጡር መሆን አለበት፡፡ እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር ግን የአውሮፓ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች እንዲህ
አይነት ዘገባ አያቀርቡም፡፡
ወገንተኛነት የሚስተዋልባቸው የጋዜጣ ሪፖርቶች፣
የሬድዮ የቀጥታ የስፖርት ስርጭቶች፣ እና የቴሌቪዥን ውይይቶችም የተለመዱ ሆነዋል፡፡ እነዚህን ዝግጅቶች የሚከታተሉ ሰዎች እከሌ
የተባለው ጋዜጠኛ እከሌ ቡድን ደጋፊ ነው፣ እከሌ ደግሞ የእከሌን ቡድን ይጠላዋል ብለው በእርግጠኝነት መናገር እስኪችሉ ድረስ እነዚህ
ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸው ዘገባዎች አሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ተረስቶ
ከጨዋታው ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች በበለጠ ትኩረት ሲዘገቡ ይስተዋላል፡፡ እከሌ የተባለው አንድ የአውሮፓ ክለብ ተጫዋች የሴት ጓደኛ
ስትደሰት እና ስትበሳጭ ምን እንደምታደርግ ጠቀመውም አልጠቀመውም ለኢትዮጵያዊ ስፖርት ተከታታይ ይቀርብለታል፡፡ አሁንም ጠቀመውም
አልጠቀመው ስለተጫዋቹ አባት፣ እናት እና ሌሎች ዘመዶች ማንነት እና ምንነት እንዲያነብ ወይንም እንዲያዳምጥ ይደረጋል፡፡
እጅግ የሚከፋው ግን እንዲህ ከላይ የጠቀስኳቸውን
ስህተቶች በሙሉ ባካተተ መልኩ የሚተገበረው የስፖርት ጋዜጠኝነት ትክክለኛው ስፖርት ጋዜጠኝነት እንደሆነ እየተወሰደ መምጣቱ ነው፡፡
አንድ ጉዳይ በተሳሳት መልኩ በተደጋጋሚ ሲተገበር እና ለየት ባለ መልኩ በተስተካከለው መንገድ ጉዳዩን የሚያቀርበው ሲጠፋ ያ የተሳሳተ
መንገድ በዘልማድ ተቀባይነት ያገኘ መንገድ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ስፖርት ጋዜጠኝነትም በዚህ መልኩ እየነጎደ ሲሆን ይኄ ሙያውንም ባለሙያውንም
ቀስ በቀስ መጉዳቱ አይቀርም፡፡
እንደኛ ጥቂት የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ባሉበት
ሃገር ከሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች አንጻር እንደ ስፖርት እና ጥበብ በመሳሰሉ እና ከመንግስትም ሆነ ሌላ አካል ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉት
ግጭት አነስተኛ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ያሉ ዘገባዎች በዚህ መልኩ ሙያዊም ክህሎትም ሆነ ስነምግባራዊ ግዴታ የጎደላቸው ሆነው ሲገኙ
የጋዜጠኞቹን እና መገናኛ ብዙሃኑን የብቃት ደረጃ ያጠያይቃል፡፡
1 comment:
fasilo..eyitah dinq new bezhu ketil.....abzagnoch gazetegnoch guadegnochih silehonu..enesum asteyayetun manbebna...megenzeb bilom tegbarawi madreg alebachew elalehu....beterefe...yigletsilih..yemil miriqat akyelihalehu....coca..nwegn...coach
Post a Comment