ፋሲለደስ

ፋሲለደስ

Saturday, April 8, 2023

የአሜሪካ ወዳጅም ጠላትም መሆን አደጋው ብዙ መሆኑን ያለፉት የቅርብ ጊዜ የበርካታ ሃገራት ታሪክ በግልፅ ያሳያል።

የቀዝቃዛው ጦርነት እጅግ በተጋጋለበት የ1960ዎቹ መጨረሻ እና የ1970ዎቹ ዓመታት ወቅት እጅግ አወዛጋቢ አና በአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከባድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረዉ ሄነሪ ኪሲንጀር በፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በተደጋጋሚ የሚወሳለት አንድ ድንቅ እውነት ተናግሯል።
ይሄውም "የአሜሪካ ጠላት መሆን አደገኛ ሊሆን ይችላል፤ የአሜሪካ ወዳጅ መሆን ግን በርግጠኝነት አጥፊ (ገዳይ) ነው" የሚለው ንግግሩ ነዉ።
"To be an enemy of America can be dangerous, but to be a friend is fatal. Henry Kissinger
ሄነሪ ኪሲንጀር በ1970ዎቹ በተለያዩ የኤዢያ፣ የአፍሪካ እና የደቡብ አሜሪካ ሃገራት አሜሪካ ታካሂድ በነበረው ጣልቃ ገብነት፣ የኮንቨርት እና ኦቨርት ስራ፣ የመንግስት ግልበጣ እና በርካታ  ቀጥተኛ እና የእጅ አዙር ጦርነቶች ዋና አርቃቂ እና ተዋናይ ስለነበረ ይሄ ንግግሩ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።
የአሜሪካ ወዳጅም ጠላትም መሆን አደጋው ብዙ መሆኑን ያለፉት የቅርብ ጊዜ የበርካታ ሃገራት ታሪክ በግልፅ ያሳያል። 
ወዳጅም ጠላትም ሳይሆኑ ኒዉትራል አቋም ይዞ መቆየቱ ላይ ነዉ ትልቁ ጥበብ። ይሄም ቢሆን እንደየሃገራቱ ፍላጎት ብቻ ላይወሰን ይችላል።
አንድ ሃገር ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለመወሰን ካላት አቅም በበለጠ አሜሪካ ከሃገሯ ጋር ያላትን ግንኙነት ለመወሰን ያላት ፍላጎት የበለጠ ተፅዕኖ አለው ።
ግኑኝነቱ በወዳጅነትም ሆነ በጠላትነት ይህ ግንኙነት ይዞት የሚመጣውን መዘዝ የሚከፍለው ግን የዛች ሃገር ህዝብ እና መንግስት ነው።
እንደ ኢትዮጵያ አይነት ትንሽ እና ደካማ ሃገር አሜሪካን ከመሰለ ግዙፍ እና እጀ ረዥም ሃገር ጋር የሚኖራት/ያላት ግንኙነት እንደ አሜሪካ ፍላጎት እና ሃገሪቱ በምታስቀምጠው ህግ እና ደምብ  እንዲሁም ቅርፅ እና ማዕቀፍ መሆኑ እሙን ነው። 
አሜሪካ ካላት አለም ዓቀፍ ተፅኖ የመፍጠር አቅም፣ እጅግ የተጋነነ ሃብት እና ቴክኖሎጂ ምንጭነት እና ወታደራዊ አቅም አንፃር ከሃገሪቱ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ግንኙነት ሳይፈጥሩ ተገልሎ መኖር ይከብዳል።
ነገር ግን የአንድን ሃገር ዉሰጣዊ ጉዳይ ባሻት መልኩ በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መልኩ ጣልቃ እንድትገባ እና ዉሳኔ ሰጪ አካል እንድትሆን መፍቀድ ይሄን ከመሰለው ግንኙነት ሊገኝ ከታሰበዉ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።
የኢትዬጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ በጎ ፈቃድ ስልጣን ላይ የወጣ መሆኑ ግልፅ የወጣ ነገር ቢሆንም በዚህ ውለታ የአድር ባይነት ባህሪውን ማጠናከሩ ዞሮ ዞሮ ህዝብ እና ሃገር እየጎዳ መሆኑን እያየን ነው። 
በተቃርኖ ጎን የቆመው እና የመንግስቱ ተገዳዳሪ ህውሃትም የአሜሪካ ተልኮ አስፈፃሚ ሆኖ መቅረቡ ችግሩን የበለጠ አወሳስቦታል።
አሁን ያለዉ የአለም ፖለቲካ እየከረረ መምጣት እና የቀዝቃዛው ጦርነት እንደገና ማገርሸት ደግሞ የኢትዬጵያን መንግስት በግልፅ ወገን ለይቶ እንዲቆም የሚያስገድደው ጊዜ እየመጣ ይመስላል። 
አሁን ካለዉ የመንግስታችን ግንኙነት እና አካሄድ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ የገባ እና ሳይወድ ተገዶ የአሜሪካን ጎራ የመረጠ ይመስላል።
ይህ ደግሞ ሊጠጋግነው ጀማምሮት የነበረውን ከኤርትራ እና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር የነበረውን ግንኙነት መልሶ ያደፈርሰዋል። 
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ምናልባትም የዕርስ በዕርስ ጦርነት በድርድርም ሆነ በአሜሪካ ተፅእኖ ሊቆም ቢችልም ሌላ እጅግ የከፋ እና አውዳሚ ጦርነት መቀስቀሱ የማይቀር ነው።
ይሄውም ከኤርትራ ወይንም ከሱዳን እና ግብፅ አሊያም ከሶስቱም ሃገራት ጋር ይሆኖል።
እንግዲህ መንግስት አስተዳደር ላይ ያለው አካል ከህዝብ እና መንግስት ጥቅም አንፃር አይቶ ከአሜሪካ ጋር የመሠረተውን ግንኙነት መፈተሽ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይመስለኝም። ካልረፈደ!

No comments:

Post a Comment