Monday, December 26, 2011

አዲስ አበባ እንዴት እና ወዴት?


አዲስ አበባ እያደገች ነው፡፡ በዚህ ነዋሪዎቿም፣ መሪዎቿም፣ ቀያሾቿም፣ አልሚዎቿም ይስማማሉ፡፡ እንዴት እና ወዴት የሚለው ግን ሁሉንም የሚያሟግት ጉዳይ ነው፡፡ ከተወሰነ ግዜ በፊት በአዲስ አበባ የከተማ ልማት እድገት ዙሪያ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመስራት አቅጄ ከላይ የጠቀስኳቸውን አራት አካላት አነጋግሬ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት የሚከተሉትን አስተያየቶች ሰጥተውኛል፡፡

ከባለሙያዎች አንጻር በርካታ ልምድ ያላቸውን አራት የሚሆኑ አርክቴክቶች ያናገርኩ ሲሆን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እይታ ነው ያላቸው፡፡ የአዲስ አበባን በፍጥነት እያደገች መሆን ሁሉም አርክቴክቶች ይስማሙበታል ነገር ግን ትክክለኛውን የእድገት ጎዳና ስለመከተሏ ጥያቄ አላቸው፡፡

እንደባለሙያዎቹ እይታ በከተማዋ የሚሰሩ ህንፃዎች የጥራት ደረጃ አጠያያቂ ነው፡፡ አንድ ህንፃ ማሟላት ከሚገባው መሰረታዊ ጉዳዮች አንጻር ቢታይ እንኳ የጣሪያ ከፍታ ማነስ፣ የአደጋ ግዜ መውጫ አለመኖር፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ አለመኖር የመሳሰሉት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት አንድ ህንፃ በአንድ ቦታ ሲሰራ የአካባቢውን አቀማመጥ፣ ታሪክ፣ ባህል እና ነዋሪ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዲዛይኑ መሰራት ሲገባው ባብዛኛው በአዲስ አበባ የሚሰሩ ህንፃዎች ከሌላ ቦታ መጥተው የበቀሉ ባዕድ ነገሮች ነው የሚመስሉት፡፡ የሃገሪቱን እና አካባቢውን እሴት ባካተተ መልኩ እየተሰሩ አይደለም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ችግር ደግሞ አብዛኞዎቹ ባለሙያዎች የህንጻ ዲዛይን ሲሰሩ ወሳኞቹ እነሱ ሳይሆኑ ደንበኞቻቸው ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የመስተዋት ህንጻ መሰራት በሌለበት ቦታ ላይ የመስታዋት ህንፃ፣ የመስተዋት ህንጻ መሰራት ባለበት ቦታ ላይ ደግሞ የብሎኬት ወይንም የሸክላ አሊያም በሌላ ጥሬ እቃ የተሰራ ህንጻ የምናገኘው፡፡ 

በአንድ አካባቢ የተሰሩ ህንጻዎችን ስንመለከት ደግሞ እርስ በእርስ የመናበብ ችግር ያለባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአንድ መስመር ላይ የሚሰሩ ህንጻዎችን ብናይ እንኳ አንዱ ህንጻ ወደ መንገድ ገባ ብሎ ሲሰራ ሌላው ከመንገድ ወጣ ብሎ፣ አንዱ በብሎኬት፣ አንዱ በመስተዋት፣ አንዱ በሸክላ፣ ሌላው በሴራሚክ በመሳሰሉት በተዘበራረቀ መልክ የተሰሩ ናቸው፡፡ ጎን ለጎን በቆሙ ህንጻዎች መካከል የአንዱ ህንጻ ከፍታ እጅግ ረዝሞ የሌላው ደግሞ እጅግ አጥሮ ያልተመጣጠነ የከፍታ ልዩነት የሚስተዋልባቸው ህንጻዎችንም በከተማችን በብዛት እንደሚስተዋሉ አርክቴክቶቹ ታዝበዋል፡፡ የጎንዮሽ ስፋታቸውም አንዱ እጅግ ቀጥኖ እና አንዱ ሰፍቶ ይስተዋላል፡፡ ከቀለም አንጻር ደግሞ ሁሉም የመሰለውን ቀለም የሚቀባበት ልምድ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ እንደ አርክቴክቶቹ እምነት በአንድ አካባቢ የሚሰሩ ህንጻዎች የአካባቢ ልማት ፕላንን ተከትለው መሰራት የሚገባቸው ሲሆን ይህን ፕላን ተከትለው የማይሰሩ ከሆነ ግን አሁን እንደሚስተዋለው የተዘበራረቀ እይታን ይፈጥራሉ፡፡

ህንጻ መሰራት ባለበት ቦታ ቪላ ቤት፣ ቪላ መሰራት በሚገባው ቦታ ህንጻ፣ መናፈሻ ሊሆን የሚገባው የገበያ ማዕከል ወይንም የህንፃ ቦታ የሆኑ አካባቢዎች በከተማዋ የሚደጋገሙ ናቸው፡፡ በተለይ የህዝብ መናፈሻ ወይንም አረንጓዴ ቦታ የአንድ ከተማ ሳንባ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን በአዲስ አበባ የህዝብ መናፈሻ ወይንም አረንጓዴ ቦታ ችላ ተብሏል፡፡  

ባለሙያዎቹ አዲስ አበባ ምን ትመስላለች ለሚለው ጥያቄ ይህን ትመስላለች ለማለት አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ እንደባለሙያዎቹ ገለጻ አዲስ አበባ አምስት ስድስት አይነት መልክ ያላት ሲሆን ይህን አይነት የተዘበራረቀ መልክ ያለው ከተማ በሌሎች ሃገሮች አይስተዋልም፡፡ 

የከተማዋ እድገት የሚበረታታ ቢሆንም እያደገች ያለችበት መንገድ ግን ሊጤን ይገባል ይላሉ፡፡ እንደእነሱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ህንጻ እየተሰራ ያለው በአብዛኛው በእንጨት ተሰርተው የነበሩ ያረጁ እና የደከሙ ቤቶች እየፈረሱ ሲሆን ይህ የሚያስከፍለው ዋጋ አነስተኛ ነው ነገር ግን የህንጻ አሰራራችን እና የአከባቢ ልማት እድገቱ በዚህ መልክ ከቀጠለ ይህን ለማስተካከል ወደፊት ህንጻዎችን ማፍረስ ሊጠበቅብን ነው ይህ ደግሞ እጅግ ውድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡

ከዚህ በፊት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በብሄራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ እንደሰማሁት ከተማዋ ብዙ አይነት መልክ እንዳላት እና የመንግስታቸው ጥረትም ቢያንስ ሁለት መልክ ያላት ከተማ ለማድረግ መጣር እንደሆነ ነው፡፡ ይህን የእርሳቸውን አስተያየት ከሰማሁ በፊትም ሆነ ከግዜያት በሗላ በከተማዋ የተለያዩ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን በተለይ የመንገድ እና የኮንዶሚኒየም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በተለያዩ የከተማዋ ዝቅተኛ መንደሮች እንዲፈርሱ እና ለባለሃብት እንዲሰጡ ወይንም ሌላ ልማት እንዲከናወንባቸው እየተደረገ ነው፡፡ ያነጋገርኳቸው የከተማ ልማት ባለስልጣናት ይህ እንቅስቃሴ መንግስት ለከተማዋ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እሰራ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡  

በህንጻ ዲዛይን እና የአካባቢ ልማት እድገት ዙሪያ ባለሙያዎች ለሚያነሱት ጥያቄ ግን ለራሳቸው ለባለሙያዎቹ ነጻነት ለመስጠት እና ፈጠራን ለማበረታታት ስንል ያደረግነው ነው የሚሉት፡፡ ያም ሆኖ የከተማዋ እድገት የተዘበራረቀ ነው ለሚለው ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው ሲሆን እንደ ባለስልጣናቱ እምነት ከተማዋ በትክክለኛ የእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ በከተማዋ የሚስተዋሉ አንድ አንድ ችግሮች የባለሙያዎች እና ባለሃብቶች ችግሮች ናቸው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ባለሃብት ህንጻ ሲያሰራ አረንጓዴ ቦታ መተው ሲገባው ያለክፍት ቦታ ሙሉ ለሙሉ ህንጻ የሚያሰራ ከሆነ ችግሩ የባለሃብቱ ነው ይላሉ፡፡

አብዛኞቹ ባለሃብቶች ህንጻ ለመስራት ቦታ በሊዝ መግዛት የሚጠበቅባቸው ሲሆን የሊዝ ዋጋ ውድ መሆን በሚሰሩት ህንጻ የጥራት ደረጃ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ዋጋ በሊዝ መሬት ከገዙ የገዙትን መሬት ሙሉ ለሙሉ “በአግባቡ” ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና መንግስት ለአረንጓዴም ሆነ ለመኪና ማቆሚያ በሚል ከሚሸጥላቸው ቦታ ላይ ከሊዝ ነጻ የሚሰጣቸው እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም አርንጓዴ ቦታ መተው ውድ ዋጋ ያወጡለትን ቦታ እንደማባከን እንደሚቆጥሩት ነው የገለጹት፡፡

የባለሙያዎች የመወሰን አቅም ማነስ ከባለሃብቶች በሚመጣ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳልሆነም አስተባብለዋል፡፡ በእርግጥ ውጭ ያዩትን ህንጻ ዲዛይን አይነት በአዲስ አበባ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት ግን የጥሬ እቃ በቅርብ እና በርካሽ መገኝት፣ የህንጻው በፍጥነት ማለቅ እና ቶሎ አገልግሎት ላይ መዋል የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

አንድ አንድ ባለሃብቶች የሚያሰሩትን ህንጻ ኮንትራክት ደረጃውን ላልጠበቀ ተቋራጭ መስጠት በህንጻዎች ዲዛይን እና ግንባታ ወቅት ለሚያጋጥሙ መሰረታዊ ችግሮች እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ የባለሃብቶቹ እርስ በእርስ አለመናበብም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የከተማዋ ነዋሪዎች የአዲስ አበባን እድገት በበጎ አይን ቢመለከቱትም እድገቱ መሰረታዊ ችግሮቻቸውን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በሚፈታ መልክ አለመሆኑ ይበልጥ ያሳስባቸዋል፡፡ በመንግስት በኩል ነዋሪዎችን የቤት እጥረት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እተደረገ መሆኑ ቢነገርም ከፍተኛ መኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ለልማት በሚል በርካታ መንደሮች እየፈረሱ ሲሆን እነዚህ መንደሮች ሲፈርሱ የነዋሪዎቹን ችግር ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታ በሚችል መልኩ ቢሰራ መልካም ነው ይላሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግ በቂ ዋስትና አለማግኘት እንዲሁም የሚሰጣቸውን ምትክ ኮንዶሚኒየም ለመግዛት አቅም ማነስ፣ ሲኖሩበት ከነበረው ቦታ አንጻር ከሚያከናውኑት ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴ ጋር እጅግ የማይጣጣም ቦታ መመደብ የመሳሰሉ ችግሮች ጎልተው እንደሚታዩም በምሬት ጭምር ገልፀውልኛል፡፡ 

ነዋሪዎቹ እና ባለሙያዎቹ በይበልጥ ትኩረት የሰጡበት ጉዳይ የከተማ ልማት እድገት መንገድ እና ህንጻ ግንባታ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን የነዋሪውን እና ሰራተኛውን ዘርፈብዙ እንቅስቃሴ በሚያሳልጥ መልኩ ሰው ተኮር የከተማ ልማት እድገት ቢሆን መልካም መሆኑን ነው፡፡

Thursday, December 15, 2011

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት እና ተግባራዊው እውነታ


በመሰረቱ ስፖርት ሲባል ባህላዊውንም ዘመናዊውንም ጨምሮ አብዛኛዎቻችን ልንዘረዝራቸው የምንችላቸው የአካል እንቅስቃሴ እና ጥልቅ እሳቤን የሚጠይቁ ሁሉንም አይነት ጨዋታዎች ያጠቃልላል፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን ፍላጎት አንጻር ስፖርት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የቆየ የመዝናኛ ፕሮግራም ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ ከመዝናኛነትም ያለፈ ጉዳይን እየሆነ ይገኛል፡፡


ስፖርት እንደ አንድ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ሲሆን ሊሰጠው የሚገባው ግምትም ያን ያህል እየከበደ መጥቷል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮች ብቻ የሚተነትኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ ሁሉ ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች፣ ሬድዮኖች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ-ገጾች እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በርካታ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያም ስፖርታዊ ጉዳይን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች እና ድረ-ገጾች ያሉ ሲሆን በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ለስፖርታዊ ጉዳዮች ከሌሎቹ ርዕሰ-ጉዳዮች አንጻር ተመጣጣኝ ባይሆንም ፍትሃዊ የአየር ሰዓት ተመድቧል ማለት ይቻላል፡፡


እዚህ ላይ ግን ከበርካታ በዙሪያየ ካሉ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶችን አደምጣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዋናው ጉዳያቸው ስፖርት ይመስል ወሪያቸው ሁሉ ስፖርት ሆነ የሚሉ አሉ፡፡ በእውነትም ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮችን እና ስፖርትን በአንድ ላይ ጨፍልቆ ለሚያቀርብ የሬድዮ ወይንም የቴሌቪዥን ጣቢያ ስፖርት ይህን ያህል የአየር ሰዓት ማግኘቱ የቀደመውን አስተያየት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ነገርግን ስፖርት በራሱ ካለው ዘርፈ ብዙ ጉዳይ አንፃር እንዲያውም ከላይ ከጠቀስኳቸው ሶስቱ ዋና ጉዳዮች ጋር መጨፍለቁ ተገቢዉን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ እንደሌሎች ሃገራት ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚያቀርቡ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አለመኖራቸው ተጎጂ እንዳደረገን አምናለሁ፡፡


ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሃገር ቤት እየተተገበረ ያለው የስፖርት ጋዜጠኝነት ምን ያህል ሙያዊ እና ስነምግባራዊ ነው ለሚለው እኔም በርካታ አሉታዊ አስተያየቶች አሉኝ፡፡


በአብዛኛው ለሃገርቤት መገናኛ ብዙሃን ስፖርት ማለት የእግር ኳስ ጨዋታ ሆኗል ያውም የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ ካለው አዝናኝነት፣ ከተመልካቹ ብዛት እና ከሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር በጋዜጣ ላይ የሰፋውን ቦታ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የበዛውን የአየር ሰዓት ቢይዝ የጎላ ጥያቄ ላያስነሳ ይችላል፡፡ ሆኖም በእኔ ዳሰሳዊ ግምት በተለያየዩ የኤፍ ኤም እና የኤ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ከሚቀርቡ የስፖርት ዝግጅቶች ብዙውን ግዜ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ እና አንድ አንድ ግዜ ከዘጠና በመቶ በላይ  የእግር ኳስ ጉዳይ የሚተነተን ሲሆን ከዚህም የሚበዛው የአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ ጉዳይ ነው፡፡


ይህ የሆነበት ምክንያት በተለያዩ ጉዳዮች ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል አንደኛ የእግር ኳስ በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ከሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተሻለ አዝናኝ ነው ተብሎ ስለሚገመት፤ ሁለተኛ በሃገር ውስጥ አብዛኛው የስፖርት አድናቂ ማህበረሰብ የእግር ኳስን በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታን የበለጠ ይወዳል ተብሎ ስለሚገመት፣ ሦስተኛ ደግሞ በተለይ ከአውሮፓ ሃገራት መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ እጅግ ብዛት ያላቸው እና የየክለቦቻቸውን ሁኔታ የሚተነትኑ መረጃዎች በተትረፈረፈ ሁኔታ ማግኘት መቻሉ የጋዜጠኞችን ትኩረት በመሳቡ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኝ ሆኗል፡፡


የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ መተንተኑ ባይከፋም መገናኛ ብዙሃኑን በሚከታተለው ህብረተሰብ ዘንድ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ግን የተስተዋለ አሊያም በደንብ የተጠና አይመስለኝም፡፡ መረጃ ስለተገኘ ዝም ብሎ መተንተን ወይንም በመገናኛ ብዙሃን ማቅረብ ፋይዳው ምንድነው? እከሌ የሚባለው ቡድን አሸነፈ ወይንም ተሸነፈ መባሉ መልካም ሆኖ ሳለ የእከሌው ቡድን ተጫዋች ወይንም አሰልጣኝ እንዲህ አለ ተብሎ መቅረቡ ለኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ተከታታዮች ጥቅሙ ምንድን ነው? እሱ እንዲህ ስላለ እና ምን ይሁን? ከዘገባው ጀርባ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚቻል ከሆነ የዘገባው ፋይዳ (impact) ተለይቷል ማለት ነው ሆኖም የአብዛኞቹ ዘገባዎች ፋይዳ ምን ስለመሆኑ አቅራቢዎቹም ተከታታዮቹም ስለማወቃቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡


በሚገርም ሁኔታ በአንድ አንድ የሃገር ውስጥ የስፖርት ጋዜጦች ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ጉዳዮች የሚቀርብባቸው ሲሆን የጋዜጣው ባለቤት አቋሙን በሚገልጽበት ኤድቶሪያል ላይ ግን ስለኢትዮጵያ ስፖርት አቋሙን ያቀርባል፡፡ በዘገቡት ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ሙያዊም ሞራላዊም ሲሆን ባልዘገቡት ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ግን አሁንም የዘገባ ፋይዳ የቱን ያህል እንደሆነ አለመረዳት ይመስለኛል፡፡


የሃገር ውስጥ ስፖርት የእግር ኳሱን ጨምሮ በአብዛኞቹ ስፖርታዊ ጉዳዮችን በሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡ ይሄን ጉዳይ ቢያቀርቡ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ስለመቻላቸውም እርግጠኞች አይደሉም፡፡ በአንድ ወቅት የደከመ ወይንም የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግብ ሚናቸውን ባልለየ መልኩ ከመጯጯህ እና አስተያየት ከመስጠት ባለፈ በአዘቦት ግዜያት የሃገር ውስጥ ስፖርት በሃገር ውስጥ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ችላ እንደተባለ ነው፡፡


ከዘህ በተረፈ ግን የሩጫ፣ የቴንስ፣ የቦሊቦል፣ የጎልፍ፣ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የገበጣ ጨዋታ እና የሌሎችም ስፖርታዊ ጨዋታዎች አድናቂዎች እነዚህን ዘገባዎች ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለማግኘት ቢያንስ በወር አንዴ መጠበቅ አሊያም ራሳቸው ጨዋታዎቹ የሚካሄዱባቸው ቦታዎች በመሄድ ከቦታው መረጃ ማግኘት ግድ ሳይላቸው አልቀረም፡፡ 


የስፖርት እና የጥበብ (ART) ጋዜጠኝነት ከሌላው የጋዜጠኝነት ሙያ በተለየ እና በተሻለ መልኩ ለጋዜጠኛው የሚሰጠው ነጻነት እና መብት አለ እሱም ሙያው ጋዜጠኞቹ በሚዘግቡት ጉዳይ ላይ የግል አስተያየታቸውን እንዲሁም ትችታቸውን በማካተት ማቅረብ እንዲችሉ መፍቀዱ ነው፡፡ 


ይህ ጋዜጠኞቹ ሊያቀርቡት የሚችሉት የግል አስተያየት እና ትችት በጉዳዮቹ መሰረታዊ ሃሳብ እና እውነታ ላይ ተነስተው የተደራጀ እና ከስሜት የፀዳ ሃሳብ ከመስጠት ስሜታዊ አስተያየት እስከመስጠት እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ ስፖርት ጋዜጠኛ አንድን የእግር ኳስ ተጫዋች “ይህ ተጫዋች የእግር ኳስ ከሚጫወት ቢያርስ ይሻል ነበር” እስከሚል ስሜታዊ አስተያየት ቢሰጥ በህግም በሥም ማጥፋት ሊያስጠይቀው አይችልም፡፡ 


ሆኖም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስፖርት የሚሉት እግር ኳስ ብቻ እንደሆነ እና እግር ኳሱም ያለው በአውሮፓ ክለቦች ዘንድ እንደሆነ እንቀበለው ብንልም እንኳ ይህንኑ የአውሮፓ ክለቦች እግር ኳስ የሚዘግቡበት መንገድም ግን የተሳሳተ ነው፡፡


የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል አንድ አንዶቹ የስፖርት ጋዜጠኞች “እኔ ብሆን ኖሮ ተጨዋቹ እንዲህ አደርግ ነበር፤ እኔ ብሆን ኖሮ አሰልጣኙ እንዲህ አይነቱን የጨዋታ አይነት እከተል ነበር” የመሳሰሉትን አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ይሄ የጋዜጠኝነት ሚናን አለመለየት ነው፡፡ አሱ ጨዋታው እንዴት እንደተካሄደ፣ ምን ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደነበሩት፣ ምን ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር መረጃ አጠናቅሮ እና የራሱን አስተያየት አክሎ ሊነግረን ሲገባ እርሱ ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማውራቱ ማንነቱን ያለመለየቱ ችግር ይመስለኛል፡፡ 


ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስፖርት ዘገባዎች ላይ እውነታም አስተያየትም ያሆኑ ጉዳዮች ሲቀርቡ ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል “እከሌ የተባለው አሰልጣኝ እንደዚህ አስቦ ነበር፣ እከሌ የተባለው ተጫዋች ፍላጎት እንዲህ ነበር” የመሳሰሉ ነገሮች በስፖርት ጋዜጦች ተፅፈው ማንበብ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲነገሩ ማዳመጥ አዲስ አይደለም፡፡ በዚህ ግዜ እኔ የጋዜጠኞቹን ሰብዓዊ ፍጡርነት እጠራጠራለሁ፡፡ አንድ አሰልጣኝ የተናገረውን ለማወቅ ጋዜጠኛ መሆን በቂ ሲሆን ይህ አሰልጣኝ ያሰበውን ለማወቅ ግን አንድም አሰልጣኙ ይህን አስቢያለሁ ብሎ መናገር አለበት አንድም ጋዜጠኛው ሰው የሚያሰበውን የሚያውቅ የተለየ ፍጡር መሆን አለበት፡፡ እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር ግን የአውሮፓ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች እንዲህ አይነት ዘገባ አያቀርቡም፡፡


ወገንተኛነት የሚስተዋልባቸው የጋዜጣ ሪፖርቶች፣ የሬድዮ የቀጥታ የስፖርት ስርጭቶች፣ እና የቴሌቪዥን ውይይቶችም የተለመዱ ሆነዋል፡፡ እነዚህን ዝግጅቶች የሚከታተሉ ሰዎች እከሌ የተባለው ጋዜጠኛ እከሌ ቡድን ደጋፊ ነው፣ እከሌ ደግሞ የእከሌን ቡድን ይጠላዋል ብለው በእርግጠኝነት መናገር እስኪችሉ ድረስ እነዚህ ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸው ዘገባዎች አሉ፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ተረስቶ ከጨዋታው ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች በበለጠ ትኩረት ሲዘገቡ ይስተዋላል፡፡ እከሌ የተባለው አንድ የአውሮፓ ክለብ ተጫዋች የሴት ጓደኛ ስትደሰት እና ስትበሳጭ ምን እንደምታደርግ ጠቀመውም አልጠቀመውም ለኢትዮጵያዊ ስፖርት ተከታታይ ይቀርብለታል፡፡ አሁንም ጠቀመውም አልጠቀመው ስለተጫዋቹ አባት፣ እናት እና ሌሎች ዘመዶች ማንነት እና ምንነት እንዲያነብ ወይንም እንዲያዳምጥ ይደረጋል፡፡


እጅግ የሚከፋው ግን እንዲህ ከላይ የጠቀስኳቸውን ስህተቶች በሙሉ ባካተተ መልኩ የሚተገበረው የስፖርት ጋዜጠኝነት ትክክለኛው ስፖርት ጋዜጠኝነት እንደሆነ እየተወሰደ መምጣቱ ነው፡፡ አንድ ጉዳይ በተሳሳት መልኩ በተደጋጋሚ ሲተገበር እና ለየት ባለ መልኩ በተስተካከለው መንገድ ጉዳዩን የሚያቀርበው ሲጠፋ ያ የተሳሳተ መንገድ በዘልማድ ተቀባይነት ያገኘ መንገድ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ስፖርት ጋዜጠኝነትም በዚህ መልኩ እየነጎደ ሲሆን ይኄ ሙያውንም ባለሙያውንም ቀስ በቀስ መጉዳቱ አይቀርም፡፡ 


እንደኛ ጥቂት የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ባሉበት ሃገር ከሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች አንጻር እንደ ስፖርት እና ጥበብ በመሳሰሉ እና ከመንግስትም ሆነ ሌላ አካል ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉት ግጭት አነስተኛ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ያሉ ዘገባዎች በዚህ መልኩ ሙያዊም ክህሎትም ሆነ ስነምግባራዊ ግዴታ የጎደላቸው ሆነው ሲገኙ የጋዜጠኞቹን እና መገናኛ ብዙሃኑን የብቃት ደረጃ ያጠያይቃል፡፡