Monday, December 26, 2011

አዲስ አበባ እንዴት እና ወዴት?


አዲስ አበባ እያደገች ነው፡፡ በዚህ ነዋሪዎቿም፣ መሪዎቿም፣ ቀያሾቿም፣ አልሚዎቿም ይስማማሉ፡፡ እንዴት እና ወዴት የሚለው ግን ሁሉንም የሚያሟግት ጉዳይ ነው፡፡ ከተወሰነ ግዜ በፊት በአዲስ አበባ የከተማ ልማት እድገት ዙሪያ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመስራት አቅጄ ከላይ የጠቀስኳቸውን አራት አካላት አነጋግሬ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት የሚከተሉትን አስተያየቶች ሰጥተውኛል፡፡

ከባለሙያዎች አንጻር በርካታ ልምድ ያላቸውን አራት የሚሆኑ አርክቴክቶች ያናገርኩ ሲሆን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እይታ ነው ያላቸው፡፡ የአዲስ አበባን በፍጥነት እያደገች መሆን ሁሉም አርክቴክቶች ይስማሙበታል ነገር ግን ትክክለኛውን የእድገት ጎዳና ስለመከተሏ ጥያቄ አላቸው፡፡

እንደባለሙያዎቹ እይታ በከተማዋ የሚሰሩ ህንፃዎች የጥራት ደረጃ አጠያያቂ ነው፡፡ አንድ ህንፃ ማሟላት ከሚገባው መሰረታዊ ጉዳዮች አንጻር ቢታይ እንኳ የጣሪያ ከፍታ ማነስ፣ የአደጋ ግዜ መውጫ አለመኖር፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ አለመኖር የመሳሰሉት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት አንድ ህንፃ በአንድ ቦታ ሲሰራ የአካባቢውን አቀማመጥ፣ ታሪክ፣ ባህል እና ነዋሪ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዲዛይኑ መሰራት ሲገባው ባብዛኛው በአዲስ አበባ የሚሰሩ ህንፃዎች ከሌላ ቦታ መጥተው የበቀሉ ባዕድ ነገሮች ነው የሚመስሉት፡፡ የሃገሪቱን እና አካባቢውን እሴት ባካተተ መልኩ እየተሰሩ አይደለም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ችግር ደግሞ አብዛኞዎቹ ባለሙያዎች የህንጻ ዲዛይን ሲሰሩ ወሳኞቹ እነሱ ሳይሆኑ ደንበኞቻቸው ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የመስተዋት ህንጻ መሰራት በሌለበት ቦታ ላይ የመስታዋት ህንፃ፣ የመስተዋት ህንጻ መሰራት ባለበት ቦታ ላይ ደግሞ የብሎኬት ወይንም የሸክላ አሊያም በሌላ ጥሬ እቃ የተሰራ ህንጻ የምናገኘው፡፡ 

በአንድ አካባቢ የተሰሩ ህንጻዎችን ስንመለከት ደግሞ እርስ በእርስ የመናበብ ችግር ያለባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአንድ መስመር ላይ የሚሰሩ ህንጻዎችን ብናይ እንኳ አንዱ ህንጻ ወደ መንገድ ገባ ብሎ ሲሰራ ሌላው ከመንገድ ወጣ ብሎ፣ አንዱ በብሎኬት፣ አንዱ በመስተዋት፣ አንዱ በሸክላ፣ ሌላው በሴራሚክ በመሳሰሉት በተዘበራረቀ መልክ የተሰሩ ናቸው፡፡ ጎን ለጎን በቆሙ ህንጻዎች መካከል የአንዱ ህንጻ ከፍታ እጅግ ረዝሞ የሌላው ደግሞ እጅግ አጥሮ ያልተመጣጠነ የከፍታ ልዩነት የሚስተዋልባቸው ህንጻዎችንም በከተማችን በብዛት እንደሚስተዋሉ አርክቴክቶቹ ታዝበዋል፡፡ የጎንዮሽ ስፋታቸውም አንዱ እጅግ ቀጥኖ እና አንዱ ሰፍቶ ይስተዋላል፡፡ ከቀለም አንጻር ደግሞ ሁሉም የመሰለውን ቀለም የሚቀባበት ልምድ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ እንደ አርክቴክቶቹ እምነት በአንድ አካባቢ የሚሰሩ ህንጻዎች የአካባቢ ልማት ፕላንን ተከትለው መሰራት የሚገባቸው ሲሆን ይህን ፕላን ተከትለው የማይሰሩ ከሆነ ግን አሁን እንደሚስተዋለው የተዘበራረቀ እይታን ይፈጥራሉ፡፡

ህንጻ መሰራት ባለበት ቦታ ቪላ ቤት፣ ቪላ መሰራት በሚገባው ቦታ ህንጻ፣ መናፈሻ ሊሆን የሚገባው የገበያ ማዕከል ወይንም የህንፃ ቦታ የሆኑ አካባቢዎች በከተማዋ የሚደጋገሙ ናቸው፡፡ በተለይ የህዝብ መናፈሻ ወይንም አረንጓዴ ቦታ የአንድ ከተማ ሳንባ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን በአዲስ አበባ የህዝብ መናፈሻ ወይንም አረንጓዴ ቦታ ችላ ተብሏል፡፡  

ባለሙያዎቹ አዲስ አበባ ምን ትመስላለች ለሚለው ጥያቄ ይህን ትመስላለች ለማለት አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ እንደባለሙያዎቹ ገለጻ አዲስ አበባ አምስት ስድስት አይነት መልክ ያላት ሲሆን ይህን አይነት የተዘበራረቀ መልክ ያለው ከተማ በሌሎች ሃገሮች አይስተዋልም፡፡ 

የከተማዋ እድገት የሚበረታታ ቢሆንም እያደገች ያለችበት መንገድ ግን ሊጤን ይገባል ይላሉ፡፡ እንደእነሱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ህንጻ እየተሰራ ያለው በአብዛኛው በእንጨት ተሰርተው የነበሩ ያረጁ እና የደከሙ ቤቶች እየፈረሱ ሲሆን ይህ የሚያስከፍለው ዋጋ አነስተኛ ነው ነገር ግን የህንጻ አሰራራችን እና የአከባቢ ልማት እድገቱ በዚህ መልክ ከቀጠለ ይህን ለማስተካከል ወደፊት ህንጻዎችን ማፍረስ ሊጠበቅብን ነው ይህ ደግሞ እጅግ ውድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡

ከዚህ በፊት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በብሄራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ እንደሰማሁት ከተማዋ ብዙ አይነት መልክ እንዳላት እና የመንግስታቸው ጥረትም ቢያንስ ሁለት መልክ ያላት ከተማ ለማድረግ መጣር እንደሆነ ነው፡፡ ይህን የእርሳቸውን አስተያየት ከሰማሁ በፊትም ሆነ ከግዜያት በሗላ በከተማዋ የተለያዩ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን በተለይ የመንገድ እና የኮንዶሚኒየም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በተለያዩ የከተማዋ ዝቅተኛ መንደሮች እንዲፈርሱ እና ለባለሃብት እንዲሰጡ ወይንም ሌላ ልማት እንዲከናወንባቸው እየተደረገ ነው፡፡ ያነጋገርኳቸው የከተማ ልማት ባለስልጣናት ይህ እንቅስቃሴ መንግስት ለከተማዋ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እሰራ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡  

በህንጻ ዲዛይን እና የአካባቢ ልማት እድገት ዙሪያ ባለሙያዎች ለሚያነሱት ጥያቄ ግን ለራሳቸው ለባለሙያዎቹ ነጻነት ለመስጠት እና ፈጠራን ለማበረታታት ስንል ያደረግነው ነው የሚሉት፡፡ ያም ሆኖ የከተማዋ እድገት የተዘበራረቀ ነው ለሚለው ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው ሲሆን እንደ ባለስልጣናቱ እምነት ከተማዋ በትክክለኛ የእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ በከተማዋ የሚስተዋሉ አንድ አንድ ችግሮች የባለሙያዎች እና ባለሃብቶች ችግሮች ናቸው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ባለሃብት ህንጻ ሲያሰራ አረንጓዴ ቦታ መተው ሲገባው ያለክፍት ቦታ ሙሉ ለሙሉ ህንጻ የሚያሰራ ከሆነ ችግሩ የባለሃብቱ ነው ይላሉ፡፡

አብዛኞቹ ባለሃብቶች ህንጻ ለመስራት ቦታ በሊዝ መግዛት የሚጠበቅባቸው ሲሆን የሊዝ ዋጋ ውድ መሆን በሚሰሩት ህንጻ የጥራት ደረጃ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ዋጋ በሊዝ መሬት ከገዙ የገዙትን መሬት ሙሉ ለሙሉ “በአግባቡ” ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና መንግስት ለአረንጓዴም ሆነ ለመኪና ማቆሚያ በሚል ከሚሸጥላቸው ቦታ ላይ ከሊዝ ነጻ የሚሰጣቸው እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም አርንጓዴ ቦታ መተው ውድ ዋጋ ያወጡለትን ቦታ እንደማባከን እንደሚቆጥሩት ነው የገለጹት፡፡

የባለሙያዎች የመወሰን አቅም ማነስ ከባለሃብቶች በሚመጣ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳልሆነም አስተባብለዋል፡፡ በእርግጥ ውጭ ያዩትን ህንጻ ዲዛይን አይነት በአዲስ አበባ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት ግን የጥሬ እቃ በቅርብ እና በርካሽ መገኝት፣ የህንጻው በፍጥነት ማለቅ እና ቶሎ አገልግሎት ላይ መዋል የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

አንድ አንድ ባለሃብቶች የሚያሰሩትን ህንጻ ኮንትራክት ደረጃውን ላልጠበቀ ተቋራጭ መስጠት በህንጻዎች ዲዛይን እና ግንባታ ወቅት ለሚያጋጥሙ መሰረታዊ ችግሮች እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ የባለሃብቶቹ እርስ በእርስ አለመናበብም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የከተማዋ ነዋሪዎች የአዲስ አበባን እድገት በበጎ አይን ቢመለከቱትም እድገቱ መሰረታዊ ችግሮቻቸውን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በሚፈታ መልክ አለመሆኑ ይበልጥ ያሳስባቸዋል፡፡ በመንግስት በኩል ነዋሪዎችን የቤት እጥረት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እተደረገ መሆኑ ቢነገርም ከፍተኛ መኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ለልማት በሚል በርካታ መንደሮች እየፈረሱ ሲሆን እነዚህ መንደሮች ሲፈርሱ የነዋሪዎቹን ችግር ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታ በሚችል መልኩ ቢሰራ መልካም ነው ይላሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግ በቂ ዋስትና አለማግኘት እንዲሁም የሚሰጣቸውን ምትክ ኮንዶሚኒየም ለመግዛት አቅም ማነስ፣ ሲኖሩበት ከነበረው ቦታ አንጻር ከሚያከናውኑት ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴ ጋር እጅግ የማይጣጣም ቦታ መመደብ የመሳሰሉ ችግሮች ጎልተው እንደሚታዩም በምሬት ጭምር ገልፀውልኛል፡፡ 

ነዋሪዎቹ እና ባለሙያዎቹ በይበልጥ ትኩረት የሰጡበት ጉዳይ የከተማ ልማት እድገት መንገድ እና ህንጻ ግንባታ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን የነዋሪውን እና ሰራተኛውን ዘርፈብዙ እንቅስቃሴ በሚያሳልጥ መልኩ ሰው ተኮር የከተማ ልማት እድገት ቢሆን መልካም መሆኑን ነው፡፡

No comments:

Post a Comment