ፋሲለደስ

ፋሲለደስ

Saturday, April 8, 2023

በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓለማችንን ሊያጠፉ የሚችሉ ስጋቶች (Existential threats)

ስመ ጥሩዉ ይሁዲ አሜሪካዊ የቋንቋ እና የፖለቲካል ፍልስፍና ሊቅ ኖም ቾምስኪ በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓለማችንን ሊያጠፉ የሚችሉ ስጋቶች (Existential threats) እውን ወደ መሆን እየተቃረቡ እንደሆነ በተለያዩ ፅሁፎቹ እና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ደጋግሞ አሳስቧል። 
ይሄውም አየር(የተፈጥሮ) ፀባይ ለውጥ እና የኒኩለር ጦርነት ናቸው። 
ቾምስኪ ሁለቱም ዓለማችንን ሊያጠፉ የሚችሉት እነዚህ ስጋቶች ተያያዥ እና መንስዔውም አንድ እንደሆነ ያትታል። 
መንስዔዉም የኒዮሊበራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት መስፋፋት ይሄን ተከትሎ እየሰፈነ የመጣው የኢምፔሪያሊዝም የአስተዳደር ስርዓት እንደሆነ ያስረዳል።
ኒዬሊበራልዚም የፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረቱ "ነፃ ገበያ" መር የንግድ ስርዓት ሲሆን ይሄን ተመክቶ በዓለም ላይ ያለ ሀብትን እና የገንዘብ ተቋምን መቆጣጠር ነው።
እንደ ቾምስኪ ትንታኔ "ነፃ ገበያ" እንደ ስሙ መጀመሪያ "ነፃ" ሳይሆን በብዙ ሸር የታጀበ የመንግስትን እና የህዝብን ሀብት ወደ ግል ንብረትነት ለማዞር ያለመ እና የገንዘብ ተቋማትን ለመቆጣጠር ያለመ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ነው። 
ይሄን ለማስፈፀም ደግሞ ሃያላን ሀገራት ባቋቋሙት እንደ የተባበሩት መንግስታት፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም፣ የዓለም ንግድ ድርጅት፣ የአውሮፖ ህብረት የመሳሰሉ ግዙፍ ድርጅቶች አጋፋሪነት ከተለያዩ ጠንካራ እና ደካማ ሀገሮች ዘንድ በሚገባ ውል የቁጥጥር መንገዱን ያሰፋል።
ደካማ ሀገራት ከእነዚህ ሃያላን ሃገራት ጋር በሚገቡት ውስብስብ ውል የሀገር ውስጥ ገበያቸውን እና የገንዘብ ተቋማቸውን ለሃያላን ሀገራት ግዙፍ ኩባንያዎች ክፍት እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።
ከዚህም አልፎ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን ከችጋር እና ይሄን ተከትሎ ሊመጣ ከሚችል አለመረጋጋት ሊያድን የሚችል የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ፖሊሲ የማውጣት ነፃነታቸውን ያጣሉ። 
ይሄንን አስገዳጅ ዓለም ዓቀፍ ውል ተገን አድርገው የሚመጡ የሃያላን ሃገራት እጅግ ግዙፍ ኩባንያዎችም በቀላሉ ወደ ደካማ ሀገራት ስለሚገቡ እና ስር ስለሚሰዱ የሀገሪቱን ሀብት እና የገንዘብ ተቋም ሀገር ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ታዳጊ ኩባንያዎችን በቀላሉ በማሸነፍ እና ከውድድር በማስወጣት ይቆጣጠሩታል።
የአንድን ደካማ ሀገር ሀብት እና የገንዘብ ተቋም ከተቆጣጠርክ ደግሞ የሀገሯን ፖለቲካ በተፈለገው የፖለቲካ ቅርፅ እና ማዕቀፍ ለማደራጀት ምቹ ይሆናል። 
ይሄም ኢምፔሪያሊዝም እንዲሰፍን የሚያደርግ እና የአንድን ሀገር ጥሬ ሀብት የበለጠ ለመበዝበዝ እና ሙሉ የሀገሪቱን ሀብት ለእነዚህ እጅግ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማዳበሪያነት ለማዋል እንዲጠቀሙበት ያደርጋል። 
ይህ ዞሮ ዞሮ ለበለጠ የአካባቢ ብክለት እና የአየር(ተፈጥሮ) ፀባይ ለውጥ አደጋ እንዲሁም ድህነት እና ይሄን ተከትሎ ለሚመጣ አለመረጋጋት ስለሚዳርግ ሀገሪቷን እና ህዝቧን የበለጠ ያደቃታል።
በአንድ ሀገር በአየር(የተፈጥሮ) ፀባይ ለውጥ እና አለመረጋጋት ምክንያት የሚመጣ ድህነት ደግሞ ለበለጠ ቁጥጥር እና የሀብት ምዝበራ ስለሚዳርግ ውጤቱ በመጀመሪያ ደረጃ ችግሩ ወደ ተፈጠረበት ምክንያት ይመራናል።
የበለጠ የሀብት እና የገንዘብ ተቋማት ቁጥጥር እና ኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት! 
ይሄን እጅግ የተወሳሰበ መሠሪ የዓለም ስርዓት የሚቃወሙ ሀገራት እና መንግስታትን ደግሞ ከላይ የጠቀስኳቸው ዓለም ዓቀፍ ተቋማት(ድርጅቶች) እርዳታ እና ብድር በመከልከል፣ ማዕቀብ በማድረግ፣ የሀገር ውስጥ ገበያን በማዛባት እና ከዚህም የባሰ ሴራ በመጎንጎን ወደ ተፈለገው የድህነት ቀለበት እንዲገቡ ያስገድዳሉ።
የሀገሩ ህዝብ እና መንግስት ከዚህም የበለጠ ጠንካራ ተቃውሞ እና አቋም የሚያራምድ ከሆነ ደግሞ ሀገሩን እና ህዝቡን የማዳከም ሴራው የበለጠ ግልፅ እየሆነ እና እያየለ ይሄዳል። 
ይሄም ማለት እርስ በእርስ በመከፋፈል እና በማተራመስ፣ የመንግስት ግልበጣ በማድረግ፣ አሊያም የእጅ አዙር ጦርነት በማድረግ እንዲሁም ከዚህም ሲከፋ ቀጥታ ጦር በማዝመት ሀገርህን እና ህዝብህን ሊበትኑት እና መልሶ እንዳይነሳ ሊያደርጉት ይችላሉ። 
ለዚህም ብዙ ርቀህ ሳትሄድ የእኛን ሀገር ኢትዬጵያን፣ ሊቢያን፣ ሶማሊያን፣ ሴሪያን፣ የመንን፣ ኢራቅን፣ ኮንጎን ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ኤዢያን እና የደቡብ አሜሪካ ሀገራትን ታሪክ መመርመር ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው።
ይሄን "በነፃ ገበያ" መር የንግድ ስርዓት መሠረት የሚስፋፋ ኒዬ ሊበራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍናን እና የኢምፔሪያሊዝም አስተዳደር ስርዓትን መስፋፋት በበቂ ሁኔታ የተገዳደሩ እና ሃያላን ምዕራብያዊያን ሀገራትን እየተቋቋሙ የመጡ እንደ ቻይና እና ራሺያ የመሳሰሉ ግዙፍ ሀገራት ከዚህ የድህነት ቀለበት ለመውጣት የሚያደርጉት መፍጨርጨር ደግሞ ሁለተኛውን እጅግ ከባድ ስጋት ደቅኗል። 
ሁለተኛው ከባድ ስጋት ደግሞ መጀመሪያ ላይ እንደገለፅኩት የኒኩለር ጦር መቀስቀስ ስጋት ሲሆን አሁን ሁለቱ የዓለም ክፍሎች የሚገኙበት እጅግ አደገኛ መፋጠጥ ስጋቱን ወደ እውነትነት እያቀረበው ነው።
ራሺያ በዩክሬይን የከፈተችው ጦርነት እንዲሁም ቻይና ከታይዋን ራስ ገዝ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የደረሰችበት መካረር እና ከምራብያውያን ጋር ያላቸው መፋጠጥ በማንኛውም ደረጃ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስነሳ እና የኒኩለር ጦርነቱን እውን ሊያደርግ የሚችል ነው።
በዚህ መሀል ትልቁ ጥያቄ ሃገርህን እና ህዝብህን እዴት ትታደጋለህ የሚለው ነው?! 
በርግጥ የአየር(የተፈጥሮ) ፀባይ ለውጥም ሆነ የኒኩለር ጦርነት ዜሮ ድምር ያለው መላ አለምን ሊያጠፋ የሚችል እና አንድ ሀገር እና ህዝብ ከሌላው ተነጥሎ ሊተርፍበት የማይችል ክስተት ቢሆንም እስከዚያው ወደ እዚህ አውዳሚ ጥፋት ሊመራ የሚችል መንገድን ተቋቁሞ መቆየት ማምሻም እድሜ ነው እንደሚባለው ብልህነት ነው።
ለዚህ ግን የህዝብ አንድነት እና ሠላም እጅግ እጅግ ወሳኝ ቁምነገር ሲሆን ይሄንን የሀገር አንድነት እና የህዝብ ሠላም ለማምጣት ግን ከሁሉም ወገን ቅንነት እና ታጋሽነት እንዲሁም ከግል እና የራስ ጥቅም አሻግሮ አስተዋይነት ይጠይቃል። 
በመጀመሪያ ግን ያለውን ስጋት ጠንቅቆ መረዳት እና ማስረዳት ተገቢ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ካልሆነ እያየነው እንዳለው ዓለም በእነዚህ ሁለቱ የአየር(ተፈጥሮ) ፀባይ ለውጥ እና የኒኩለር ጦርነት ምክንያት ካላት የመጥፋት ስጋት ቀድመን እንዳንከስም እሰጋለሁ።

No comments:

Post a Comment